ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 14:11-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. አራቱ ነገሥታትም በሰዶምና በገሞራ ያገኙትን ሀብትና ምግብ ሁሉ ዘርፈው ሄዱ።

12. የአብራም ወንድም ልጅ ሎጥ፣ ሰዶም ይኖር ስለ ነበር እርሱንም ማርከው ንብረቱንም ዘርፈው ሄዱ።

13. ከዚህም ያመለጠ አንድ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ይህን ነገረ፤ አብራም በዚያ ጊዜ ይኖር የነበረው በአሞራዊው መምሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ ነበር። መምሬ፣ ወንድሞቹ አስኮና አውናን የአብራም የኪዳን አጋሮቹ ነበሩ።

14. አብራም የወንድሙን ልጅ መማረክ እንደ ሰማ በቤቱ ተወልደው አድገው የሠለጠኑ 318 ጦረኞች አሰልፎ እስከ ዳን ድረስ ገሠገሠ።

15. አብራም ጠላቶቹን ለማጥቃት ሰራዊቱን ሌሊቱን በቡድን በቡድን ከፋፍሎ ከደማስቆ በስተ ሰሜን እስከሚገኘው እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው።

16. አብራም ጠላት የማረከውን በሙሉ አስጣለ፤ የወንድሙን ልጅ ሎጥን፣ ንብረቱን እንዲሁም ሴቶቹንና ሌሎቹን ምርኮኞች አስመለሰ።

17. አብራም ኮሎዶጎምርንና አብረውት የተሰለፉትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፣ የሰዶም ንጉሥ፣ “የንጉሥ ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ።

18. የልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅም እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤

19. አብራምንም እንዲህ ሲል ባረከው፤“ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑልእግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) አብራምን ይባርክ፤

20. ጠላቶችህን አሳልፎ በእጅህ የሰጠህ፣ልዑል እግዚአብሔር (ኤል-ኤልዮን) ይባረክ።”አብራምም ካመጣው ሁሉ ዐሥራትን ሰጠው።

21. የሰዶም ንጉሥም አብራምን፣ ሰዎቹን ለእኔ ስጠኝ፤ ንብረቱን ግን ለራስህ አስቀር” አለው።

22. አብራም ግን ለሶዶም ንጉሥ እንዲህ አለው፤ “ሰማይንና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ ወደ ልዑል አምላክ (ኤል-ኤልዮን) እጆቼን አንሥቻለሁ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 14