ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 5:11-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ሂዱና የራሳችሁን ጭድ ከየትም ፈልጋችሁ አምጡ፤ የሥራ ድርሻችሁ ግን ከቶ አይቀነስም’ ” አሉ።

12. ስለዚህም ሕዝቡ በጭድ ፈንታ ገለባ ለመሰብሰብ በግብፅ ምድር ሁሉ ተሰማሩ።

13. የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹም “በየዕለቱ መሥራት የሚገባችሁ ሥራ ቀድሞ ጭድ ስናቀር ብላችሁ ከምትሠሩት ሥራ ማነስ የለበትም” እያሉ ያጣድፏቸው ነበር።

14. የሥራው የቅርብ ኀላፊዎች ተደርገው በፈርዖን የባሪያ ተቈጣጣሪዎች የተመደቡት እስራኤላውያንም፣ “የትናንቱንም ሆነ የዛሬውን ሸክላ ሥራ ድርሻችሁን እንደ ቀድሞው ለምን አላሟላችሁም?” እየተባሉ ይጠየቁና ይገረፉ ነበር።

15. ከዚያም ሥራውን በቅርብ ሆነው የሚቈጣጠሩት እስራኤላውያን ኀላፊዎች ፈርዖን ፊት ቀርበው እንዲህ ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ፤ “እኛን ባሮችህን እንደዚህ የምታደርገን ለምንድን ነው?

16. ለእኛ ለባሮችህ ጭድ ሳያቀርቡልን ሸክላ ሥሩ ይሉናል፤ ጥፋቱ የገዛ ሰዎችህ ሆኖ ሳለ እኛ ባሮችህ ግን እንገረፋለን።”

17. ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ልግመኞች! እናንተ ልግመኞች! እየደጋገማችሁ እንሂድ ‘ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እንሠዋ’ የምትሉት ለዚህ ነው።

18. በሉ አሁንም ወደ ሥራችሁ ተመለሱ፤ ምንም ጭድ አይሰጣችሁም፤ ያም ሆኖ ግን የተመደበላችሁን ሸክላ ማምረት አለባችሁ።”

19. እስራኤላውያን ኀላፊዎችም፣ “በየቀኑ የምትሠሩት ሸክላ ቍጥሩ ቀድሞ ከሚሠራው ሸክላ ማነስ የለበትም” ተብሎ ሲነገራቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ተረዱት።

20. ከፈርዖን ዘንድ እንደ ተመለሱ ሲጠብቋቸው የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አግኝተው፣

21. “እግዚአብሔር (ያህዌ) ይይላችሁ፤ ይፍረድባችሁም ፈርዖንና ሹማምንቱ እንዲጠየፉን አደረጋችሁ፤ እንዲገድሉን በእጃቸው ሰይፍ ሰጣችኋቸው” አሏቸው።

22. ሙሴም ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተመልሶ፦ “አቤቱ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ መከራ ያመጣኸው ለምንድን ነው? የላክኽኝ ለዚሁ ነው?

23. በአንተ ስም እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከሄድሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ እርሱ በዚህ ሕዝብ ላይ፣ አበሳ አምጥቶአል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አልታደግኸውም” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 5