ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 5:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ‘በምድረ በዳ በዓል እንዲያደርግልኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ ይላል” አሉት።

2. ፈርዖንም “እንድታዘዘውና እስራኤልን እንድለቅለት ለመሆኑ ይህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ማነው?” እግዚአብሔርን (ያህዌ) አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም” አለ።

3. እነርሱም፣ “የዕብራውያን አምላክ (ኤሎሂም) ለእኛ ተገልጦልናል፤ የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳው ተጒዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ አለዚያ ግን በመቅሠፍት ወይም በሰይፍ ይመታናል” አሉት።

4. የግብፅ ንጉሥም፣ “እናንተ ሙሴና አሮን፤ ለምንድ ነው ሕዝቡን ሥራ የምታስፈቱት! በሉ እናንተም ወደየሥራችሁ ተመለሱ”

5. ፈርዖንም፣ “እነሆ፤ አሁን የምድሪቱ ሕዝብ እጅግ ብዙ ነው፤ እናንተም እንዳይሠሩ እያደረጋችኋቸው ነው” አለ።

6. በዚያኑ ዕለት ፈርዖን ለባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና ለሕዝቡ አለቆች እንዲህ ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤

7. “ለጡብ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ጭድ ካለበት ቦታ ሄደው ራሳቸው ያምጡ እንጂ ከእንግዲህ እናንተ እንዳታቀርቡላቸው።

8. ሆኖም ቀድሞ በሚያቀርቡት ሸክላ ልክ ሠርተው እንዲያቀርቡ አድርጓቸው። የሥራ ድርሻቸውን አትቀንሱ። ሰነፎች ናቸው፤ ‘ሄደን ለአምላካችን መሥዋዕት እንሠዋ’ የሚሉትም ለዚህ ነው።

9. ለሐሰት ወሬ ስፍራ ሳይሰጡ ተግተው እንዲሠሩ ሥራውን አክብዱባቸው።”

10. ከዚያም የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና አለቆቹ ወጥተው ለሕዝቡ፦ “ፈርዖን የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእንግዲህ ጭድ አልሰጣችሁም፤

11. ሂዱና የራሳችሁን ጭድ ከየትም ፈልጋችሁ አምጡ፤ የሥራ ድርሻችሁ ግን ከቶ አይቀነስም’ ” አሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 5