ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 38:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. በአደባባዩ መግቢያ ላይ ያለው መጋረጃ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና የጥልፍ ባለ ሙያ ከጠለፈው፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠራ ነበር፤ ቁመቱ ሃያ ክንድ፣ እንደ አደባባዩ መጋረጃዎች ከፍታው አምስት ክንድ ነበረ፤

19. አራት ምሰሶዎችና አራት መቆሚያዎች ነበሩት፤ ኵላቦቻቸውና ዘንጎቻቸው የብር ሲሆኑ፣ ጫፎቻቸው በብር ተለብጠው ነበር።

20. የማደሪያው ድንኳንና የአደባባዩ ዙሪያ ካስማዎች ሁሉ ከናስ የተሠሩ ነበሩ።

21. ለማደሪያው ድንኳን፣ ይኸውም ለምስክሩ ድንኳን ሙሴ ባዘዘው፣ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር መሪነት ሌዋውያኑ በጻፉት መሠረት የዕቃዎቹ ቍጥር ይህ ነው።

22. ከይሁዳ ነገድ የሆር የልጅ ልጅ፣ የኡሪ ልጅ የሆነው ባስልኤል፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።

23. ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ፣ ዕቅድ አውጭና የእጅ ጥበብ ባለ ሙያ፣ በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ጥልፍ ጠላፊ ነበር።

24. ለመቅደሱ ሥራ ሁሉ ከመወዝወዙ ስጦታ በመቅደሱ ሰቅል መሠረት የዋለው ጠቅላላ ወርቅ ሃያ ዘጠኝ መክሊትና ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ።

25. በቈጠራው ወቅት ተቈጥረው ከነበሩት ማኅበረሰብ የተገኘው ብር ለመቅደሱ ሰቅል አንድ መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅሎች ነበሩ፤

26. ከተቈጠሩት ጋር አብረው ከሆኑት ሃያና ከሃያ ዓመት በላይ የሆናቸው ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች የሰጡት እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን በአንድ ሰው አንድ ቤካ ይኸውም ግማሽ ሰቅል ነበረ።

27. አንድ መቶ የብር መክሊቶች የመቅደሱንና የመጋረጃዎቹን መቆሚያዎች ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር፤ ይኸውም ከአንድ መቶ መክሊቶች አንድ መቶ መቆሚያዎች ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ መቆሚያ አንድ መክሊት ማለት ነው።

28. አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅሎችን ለምሰሶዎቹ ኵላቦች፣ የምሰሶዎቹን አናት ለመለበጥና ዘንጎቻቸውንም ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር።

29. ከመወዝወዙ ስጦታ የሆነው ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ።

30. ለመገናኛው ድንኳን መግቢያ ለናስ መሠዊያው ከናስ መጫሪያው፣ ለዕቃዎቹም ሁሉ መቆሚያዎቹን ለመሥራት አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር፤

31. ለአደባባዩ ዙሪያ፣ ለመግቢያው እንዲሁም ለማደሪያው ድንኳን ካስማዎች ሁሉና ለአደባባዩ ዙሪያ ሁሉ እንዲሁ አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 38