ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 38:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱ አምስት ክንድ የሆነ ባለ ዐራት ማእዘን ነበረ።

2. ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ አራት ቀንድ ሠሩ፣ መሠዊያውንም በናስ ለበጡት።

3. ዕቃዎቹንም ሁሉ ይኸውም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መርጫ ጐድጓዳ ሳህኖቹን፣ ሜንጦዎቹንና የእሳት መያዣዎቹን ከናስ ሠሯቸው።

4. ለመሠዊያውም ከጠርዝ በታች ሆኖ ከመሠዊያው ግማሽ ቁመት ላይ የሚሆን የናስ ፍርግርግ ማንደጃ ሠሩ።

5. ለናሱ ፍርፍርግ ማንደጃ አራት ማእዘኖች መሎጊያዎቹን እንዲይዙ የናስ ቀለበቶችን ሠሩ።

6. መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሠርተው በናስ ለበጧቸው።

7. መሠዊያውን ለመሸከም በመሠዊያው ጐኖች ይሆኑ ዘንድ መሎጊያዎቹን በቀለበቶቹ ውስጥ አስገቧቸው፤ ውስጡንም ክፍት በማድረግ ከሳንቃዎች ሠሩት።

8. የናስ መታጠቢያ ሳሕንና የናስ መቆሚያውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ከሚያገለግሉት ሴቶች መስተዋት ሠሩት።

9. ቀጥሎም አደባባዩን ሠሩ፤ የደቡቡ ክፍል ርዝመት አንድ መቶ ክንድ ሲሆን፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤

10. ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የናስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹ ላይ ዘንጎች ነበሩት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 38