ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 36:12-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. በአንደኛው መጋረጃ ላይ አምሳ ቀለበቶችን በሌላው ተጋጥሞ ከተሰፋው በስተ መጨረሻ ካለው መጋረጃ ላይ አምሳ ቀለበቶችን እርስ በርሳቸው ትይዩ በማድረግ ሠሩት።

13. ከዚያም አምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሠሩ፤ የማደሪያው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድም ተጋጥመው የተሰፉትን ሁለቱን መጋረጃዎች አያያዙባቸው።

14. ከማደሪያው በላይ ለሚሆነው ድንኳን ከፍየል ቆዳ የተሠሩ በጠቅላላ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ሠሩ።

15. ዐሥራ አንዱ መጋረጃዎች ተመሳሳይ ልክ ሲኖራቸው፣ ቁመታቸው ሠላሳ ክንድ፣ ወርዳቸውም አራት ክንድ ነበር።

16. አምስቱን መጋረጃዎች በአንድ በኩል፣ ሌሎቹን ስድስት መጋረጃዎች ደግሞ በሌላ በኩል አንድ ላይ አያያዟቸው።

17. በስተ መጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን፣ በሌላ በኩል ባለው በስተ መጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ አምሳ ቀለበቶችን አበጁ።

18. ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝም አምሳ የናስ ማያያዣዎችን ሠሩ።

19. ከዚያም ለድንኳኑ መሸፈኛ የሚሆን ቀይ ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ሠሩ፤ በላዩ ላይ የሚሆንም የአቆስጣ ቆዳ አበጁ።

20. ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አበጁ።

21. እያንዳንዱም ወጋግራ ቍመቱ ዐሥር ክንድ፣ ስፋቱ አንድ ክንድ ተኩል ነበር፣

22. ትይዩ የሆኑ ሁለት ጒጦች ነበሩት፤ የማደሪያውን ድንኳን ወጋግራዎች በዚህ መልክ ሠሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 36