ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 34:4-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርቦ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶችም በእጆቹ ያዘ።

5. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐወጀ።

6. እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ አለፈ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣

7. ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።”

8. ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤

9. “አቤቱ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ (አዶናይ) ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።”

10. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው አብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ያያሉ።

11. ዛሬ የማዝህን ፈጽም፤ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን በፊትህ አስወጣቸዋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 34