ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 34:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጥረብ፤ እኔም አንተ በሰበርካቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ።

2. በማለዳ ተዘጋጅተህ ወደ ሲና ተራራ ውጣ፤ በዚያ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም፤

3. ከአንተ ጋር ማንም እንዳይመጣ ወይም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ እንዳይታይ፤ የበግና የፍየል መንጋዎች የቀንድ ከብቶችም እንኳ፣ በተራራው ፊት ለፊት መጋጥ የለባቸውም።”

4. ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርቦ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶችም በእጆቹ ያዘ።

5. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐወጀ።

6. እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ አለፈ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣

7. ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።”

8. ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤

9. “አቤቱ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ (አዶናይ) ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።”

10. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው አብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ያያሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 34