ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 33:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “አንተና ከግብፅ ያወጣኸው ሕዝብህ ይህን ስፍራ ለቃችሁ ‘ለዘርህ እሰጣለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ገባሁላችሁ ምድር ሂዱ።

2. መልአክን በፊትህ በመላክ፣ ከነዓናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያዊያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ።

3. ማርና ወተት ወደምታፈሰው ምድር ውጡ፤ ነገር ግን አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆናችሁ፣ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋር አልሄድም።”

4. ሕዝቡም እነዚህን አሳዛኝ ቃላት በሰሙ ጊዜ ይተክዙ ጀመር፤ ማንም ሰው አንዳች ጌጥ አላደረገም።

5. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “እስራኤላውያንን፣ ‘እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፤ ለአንዳፍታ እንኳ ከእናንተ ጋር አብሬአችሁ ብሄድ አጠፋችሁ ነበር፤ አሁንም ጌጣጌጦቻችሁን አውልቁ፤ እናንተን ምን ማድረግ እንዳለብኝ እወስናለሁ ብለህ ንገራቸው” አለው።

6. ስለዚህ እስራኤላውያን በኮሬብ ተራራ ላይ ጌጣጌጦቻቸውን አወለቁ።

7. ሙሴ “የመገናኛው ድንኳን” ብሎ የጠራውን በመውሰድ፣ ከሰፈሩ ውጭ ራቅ ባለ ቦታ ላይ ይተክለው ነበር። እግዚአብሔርን (ያህዌ) መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይሄድ ነበር።

8. ሙሴ ወደ ድንኳኑ በወጣ ጊዜ ሕዝቡ በመነሣት ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቁመው ይጠባበቁ ነበር።

9. ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሙሴ ጋር እየተነጋገረ ሳለ የደመናው ዐምድ ወርዶ በመግቢያው ላይ ይቆም ነበር።

10. ሕዝቡ የደመናውን ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆሞ ሲያዩት ሁሉም በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይሰግዱ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 33