ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 30:14-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከሃያ በላይ ሆኖ ወደ ተቈጠሩት ያለፉት ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸው።

15. ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ ባለ ጠጋው ከግማሽ ሰቅል በላይ፣ ድኻውም አጉድሎ አይስጥ።

16. የማስተሰረያውን ገንዘብ ከእስራኤላውያን ተቀብለህ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት አውለው፤ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የእስራኤላውያን ማስተስረያ ይሆናል።”

17. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤

18. “ለመታጠቢያ ከናስ ማስቀመጫው ጋር የናስ ሰን አብጅ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ አድርግበት።

19. አሮንና ወንዶች ልጆቹ በውስጡ ባለው ውሃ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል።

20. ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ሁሉ እንዳይሞቱ በውሃ ይታጠቡ፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የእሳት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ለማገልገል በሚቀርቡበት ጊዜ፣

21. እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠባሉ፤ ይህም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለአሮንና ለትውልዶቹ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።”

22. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፣

23. “ምርጥ ቅመሞችን፣ አምስት መቶ ሰቅል ፈሳሽ ከርቤ፣ ግማሽ ይኸውም ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል ጣፋጭ ቀረፋ፣ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል ጠጅ ሣር፣

24. አምስት መቶ ሰቅል ብርጒድ ውሰድ፤ ሁሉም እንደ መቅደሱ ሰቅልና አንድ የኢን መስፈሪያ የወይራ ዘይት ይሁን፤

25. እነዚህን በቀማሚ እንደ ተሠራ እንደሚሸት ቅመም የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት አድርግ፤ የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት ይሆናል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 30