ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 28:11-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. የቅርጽ ሠራተኛ ማኅተም እንደሚቀርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለቱ ድንጋዮች ላይ ቅረጽ፤ ከዚያም ድንጋዮቹን በወርቅ ፈርጥ ክፈፋቸው፤

12. ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ጋር አያይዛቸው፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት መታሰቢያ እንዲሆኑ አሮን ስሞቹን በትከሻው ላይ ይሸከማቸው።

13. የወርቅ ፈርጦችን አብጅ፣

14. እንደ ገመድ ያሉ ሁለት በንጹሕ ወርቅ የተጐነጐኑ ድሪዎችን አብጅተህ ከፈርጡ ጋር አያይዛቸው።

15. “የፍርድ መስጫውን የደረት ኪስ ብልኅ ሠራተኛ እንደሚሠራው አድርገህ አብጀው፤ ልክ እንደ ኤፉዱ ከወርቅ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ አብጀው።

16. ርዝመቱ አንድ ስንዝር፣ ስፋቱ አንድ ስንዝር ሆኖ ባለ አራት ማእዘንና በድርቡ የታጠፈ ይሁን።

17. ከዚያም በላዩ ላይ በአራት ረድፍ የከበሩ ድንጋዮች አድርግበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርዲዮን፣ ቶጳዝዮን፣ የሚያበረቀርቅ ዕንቁ፤

18. በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፣ ሰንፔር፣ አልማዝ፤

19. በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፣ ኬልቄዶን፣ አሜቴስጢኖስ፤

20. በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያስጴድ አድርግበት፤ በወርቅ ፈርጥም ክፈፋቸው።

21. የዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስሞች እንደ ማኅተም የተቀረጸባቸው ለእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ይሁኑ።

22. “ለደረት ኪሱ ከንጹሕ ወርቅ እንደ ገመድ ሆኖ የተጌጠ ጒንጒን አብጅለት።

23. ለእርሱም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አብጅተህ ከደረት ኪሱ ሁለት ጎኖች ጋር አያይዘው።

24. ሁለቱን የወርቅ ጒንጒኖች በደረት ኪሱ ጐኖች ላይ ካሉት ቀለበቶች ጋር አያይዛቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 28