ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 28:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ከእስራኤላውያን መካከል ወንድምህ አሮንን ከወንዶች ልጆቹ ከናዳብ፣ ከአብ ዩድ፣ ከአልዓዛርና ከኢታምር ጋር ወደ አንተ አቅርባቸው።

2. ለእርሱም ማዕረግና ክብር ለመስጠት ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን አብጅለት።

3. ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ የተለየ ይሆን ዘንድ ጥበብ ለሰጠኋቸው በዚህ ጒዳይ ላይ ጥበበኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ለአሮን መጐናጸፊያዎችን እንዲሠሩለት ንገራቸው።

4. የሚሠሯቸው መጐናጸፊያዎች የደረት ልብስ ኤፉድ ቀሚስ፣ ጥልፍ ሸሚዝ፣ ጥምጥምና መታጠቂያ ናቸው፤ ካህን ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ይሠራሉ።

5. ወርቅ፣ ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና እንዲሁም ቀጭን በፍታ ይጠቀሙ።

6. “የጥልፍ ዐዋቂዎች ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ ይሥሩት።

7. መተሳሰር እንዲችል ሆኖ፣ ዳርና ዳር ከሚገኙት ከሁለቱ ጐኖች ጋር የተያያዙ ሁለት የትከሻ ንጣዮች ይኑሩት።

8. በጥበብ የተጠለፈው የወገብ መታጠቂያ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር ከኤፉድ ጋር አንድ ወጥ ሆኖ የተሠራ ይሁን።

9. “ሁለት የመረግድ ድንጋዮች ውሰድና የእስራኤልን ልጆች ስሞቻቸውን ቅረጽባቸው።

10. እንደ ልደታቸው ቅደም ተከተል ስድስቱን ስሞች በአንዱ ድንጋይ ላይ የቀሩትንም ስሞች በሌላው ላይ ቅረጽባቸው።

11. የቅርጽ ሠራተኛ ማኅተም እንደሚቀርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለቱ ድንጋዮች ላይ ቅረጽ፤ ከዚያም ድንጋዮቹን በወርቅ ፈርጥ ክፈፋቸው፤

12. ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ጋር አያይዛቸው፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት መታሰቢያ እንዲሆኑ አሮን ስሞቹን በትከሻው ላይ ይሸከማቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 28