ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 27:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ ርዝመቱ አምስት፣ ስፋቱም አምስት ክንድ ሆኖ ባለ አራት ማእዘን ይሁን።

2. ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ ቀንድ አድርግለት፤ መሠዊያውንም በነሐስ ለብጠው።

3. ዕቃዎቹን ሁሉ ይኸውም የዐመድ ማስወገጃ ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፣ ሜንጦዎችንና የፍም መያዣዎችን ከነሐስ አብጃቸው።

4. ዐመድ ማውረጃ የሚሆን እንደ መረብ የሆነ የነሐስ ፍርግርግ አድርግለት በአራቱም የመረብ ማእዘኖች ላይ የነሐስ ቀለበቶች አብጅ።

5. እስከ መሠዊያው ወገብ እንዲደርስ በመሠዊያው ዙሪያ ባለው እርከን ሥር አድርገው።

6. የግራር ዕንጨት መሎጊያዎችን ለመሠዊያው ሠርተህ በነሐስ ለብጣቸው።

7. በሸክም ጊዜ በመሠዊያው ሁለቱም ጎኖች እንዲሆኑ፣ መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ።

8. መሠዊያውን ውስጡን ባዶ ከሆኑ ሳንቃዎች አብጀው፤ ልክ በተራራው ላይ ባየኸው መሠረት ይበጅ።

9. “ለመገናኛው ድንኳን አደባባይ አብጅለት፤ በደቡብ በኩል ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ይሁን፣ ከቀጭን በፍታ የተፈተሉ መጋረጃዎች፣

10. ሃያ ምሰሶዎች፣ ሃያ የነሐስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ይኑሩት።

11. በሰሜኑም በኩል አንድ መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይሁኑ፤ ሃያ ምሰሶዎቹ፣ ሃያ የነሐስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎችም ላይ ዘንጎች ይኑሩ።

12. “የአደባባዩ ምዕራብ ጫፍ ስፋቱ አምሳ ክንድ ሆኖ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር መቆሚያዎች ያሉት መጋረጃዎች ይኑሩት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 27