ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 25:8-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. “ከዚያም መቅደስ እንዲሠሩልኝ አድርግ፤ እኔም በመካከላቸው አድራለሁ።

9. ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያለውን ዕቃ ሁሉ ልክ እኔ በማሳይህ ዕቅድ መሠረት ሥሩት።

10. “ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር እንጨት እንዲሠሩ አድርግ።

11. ውስጡንም ውጭውንም በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አብጅለት።

12. አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ ሁለቱን በአንድ በኩል ሁለቱን በሌላ በኩል ከአራቱ እግሮች ጋር አያይዝ።

13. ከዚያም መሎጊያዎችን ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ በወርቅም ለብጣቸው።

14. መሎጊያዎችንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ማእዘኖች ላይ ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።

15. መሎጊያዎቹ ከታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ምንጊዜም መውጣት የለባቸውም።

16. የምሰጥህንም ምስክር በታቦቱ ውስጥ አኑር።

17. “ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ሥራለት።

18. በስርየት መክደኛው ዳርና ዳር ላይ የሚሆኑ ከወርቅ የተቀረጹ ሁለት ኪሩቤል ሥራ።

19. አንዱን ኪሩብ በአንደኛው፣ ሁለተኛውን ኪሩብ በሌላኛው ዳር አድርግ በሁለቱም ጫፎች ሁለቱን ኪሩቤል ከስርየት መክደኛው ጋር አንድ ወጥ አድርገህ ሥራቸው።

20. ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት የስርየት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይሸፍኑ፤ እርስ በርሳቸው ትይዩ በመሆንም ፊታቸውን ወደ ስርየት መክደኛው ያድርጉ።

21. የስርየት መክደኛውን በታቦቱ አናት ላይ አስቀምጠው፤ እኔ የምሰጥህን ምስክሩንም በታቦቱ ውስጥ አስቀምጥ።

22. በምስክሩ ታቦት ላይ ባሉት በሁለቱ ኪሩቤል መካከል፣ በስርየት መክደኛው ላይ በዚያ እኔ ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ ለእስራኤላውያን የሚሆኑትን ትእዛዞቼንም እሰጥሃለሁ።

23. ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩልጨ የሆነ ጠረጴዛ ከግራር ዕንጨት ሥራ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 25