ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 22:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. “አንድ ሰው ከብቶቹን በመስክ ወይም በወይን ቦታ አሰማርቶ እንዲሁ ስድ ቢለቃቸውና የሌላውን ሰው መስክ ቢግጡ፣ ምርጥ ከሆነው ከራሱ መስክ ወይም የወይን ቦታ መክፈል አለበት።

6. “እሳት ተነሥቶ ወደ ቍጥቋጦ ቢዘምትና ክምርን ወይም ያልታጨደን እህል ወይም አዝመራውን እንዳለ ቢበላ፣ እሳቱን ያቀጣጠለው ሰው ካሣ ይክፈል።

7. “አንድ ሰው ብሩ ወይም ንብረቱ ያለ ሥጋት ይጠበቅለት ዘንድ ለጎረቤቱ ሰጥቶ ሳለ ቢሰርቅበትና፣ ሌባው ቢያዝ እጥፍ ይክፈል፤

8. ሌባው ካልተያዘ ግን፣ የቤቱ ባለቤት በንብረቱ ስርቆት ላይ እጁ ይኑርበት ወይም አይኑርበት ይታወቅ ዘንድ ዳኞች ፊት ይቅረብ።

9. አንድ ሰው በሬን፣ አህያን፣ በግን፣ ልብስን፣ ወይም ማናቸውንም ንብረት ያለ አግባብ በባለቤትነት ይዞ ሳለ፣ ‘የኔ ነው’ ባይ ቢመጣና ክርክር ቢነሣ፣ ባለ ጉዳዮቹ ነገሩን ለዳኞች ያቅርቡት፤ ዳኞቹ ጥፋተኛ ነው ያሉትም ለጎረቤቱ እጥፉን ይክፈል።

10. “አንድ ሰው አህያ፣ በሬ፣ በግ፣ ወይም ማናቸውንም እንስሳ በጎረቤቱ ዘንድ በአደራ አስቀምጦ ሳለ እንስሳው ቢሞት፣ ወይም ጉዳት ቢደርስበት፣ ወይም ሰው ሳያይ ተነድቶ ቢወሰድ፣

11. በሁለቱ መካከል ያለው አለመግባባት መፍትሄ የሚያገኘው፣ ጎረቤቱ የሌላውን ሰው ንብረት እንዳልወሰደ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በመማል ነው። ባለቤቱም ይህን መቀበል አለበት፤ የካሣም ክፍያ አይጠየቅም።

12. እንስሳው ከጎረቤት ተሰርቆ ከሆነ ግን፣ ለባለቤቱ ካሣ መክፈል አለበት።

13. በዱር አራዊት ተበልቶ ከሆነ፣ ከአውሬ የተረፈውን ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ፣ ስለ ተበላው እንስሳ ካሣ እንዲከፍል አይጠየቅም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 22