ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 21:21-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ነገር ግን ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ባሪያው ቢነሣ መቀጣት የለበትም፤ ባሪያው ንብረቱ ነውና።

22. “በጥል ላይ ያሉ ሰዎች ነፍሰ ጡር ሴት ቢመቱና እርሷም ያለጊዜዋ ብትወልድ፣ ጉዳቱም ለክፉ የማይሰጥ ቢሆን፣ ጉዳት ያደረ ሰባት ሰው የሴትዮዋ ባል የጠየቀውንና ፈራጆቹ የፈቀዱትን ካሣ ሁሉ መክፈል አለበት።

23. ነገር ግን የከፋ ጉዳት ቢደርስ ሕይወት በሕይወት፣

24. ዓይን በዓይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በግር፣

25. ቃጠሎ በቃጠሎ፣ ቍስል በቍስል፣ ግርፋት በግርፋት ታስከፍላለህ።

26. “አንድ ሰው የወንድ ወይም የሴት አገልጋዩን ዐይን መትቶ ቢያጠፋ፣ ስለ ዐይን ካሣ አገልጋዩን ነጻ ይልቀቀው።

27. የወንድ ወይም የሴት አገልጋዩን ጥርስ ቢሰብር፣ ስለ ጥርስ ካሣ አገልጋዩን ነጻ ይልቀቀው።

28. “በሬ አንድን ወንድ ወይም ሴት ወግቶ ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ተወግሮ ይሙት፤ ሥጋውም አይበላ፤ ነገር ግን የበሬው ባለቤት በኀላፊነት አይጠየቅም።

29. ሆኖም በሬው የመውጋት ዐመል ያለበት ሆኖ ለባለቤቱም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ሳለ በበረት ሳያስቀረው ቀርቶ አንድን ወንድ ወይም ሴት ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ይወገር፤ ባለቤቱም እንዲሁ ተወግሮ ይሙት።

30. ሆኖም ካሣ እንዲከፍል ከተጠየቀ፣ የተጠየቀውን ሁሉ በመክፈል ሕይወቱን ይዋጅ።

31. አንድ በሬ አንድን ወንድ ወይም ሴት ልጅ ቢወጋ በዚሁ ሕግ መሠረት ይፈጸም።

32. አንድ በሬ ወንድ ወይም ሴት ባሪያን ቢወጋ ባለቤቱ ሠላሳ የብር ሰቅል ለባሪያው ጌታ መክፈል አለበት፤ በሬውም በድንጋይ ይወገር።

33. “አንድ ሰው ጒድጓድን ከፍቶ ቢተው፣ ወይም ጒድጓድ ቆፍሮ ሳይከድነው ቢቀርና በሬ ወይም አህያ ቢገባበት፣

34. የጒድጓዱ ባለቤት ኪሳራ ይክፈል፤ ለባለቤቱ መክፈል አለበት፤ የሞተውም እንስሳ ለእርሱ ይሆናል።

35. “የአንድ ሰው በሬ የሌላውን ሰው በሬ ወግቶ ቢገድለው፣ በሕይወት ያለውን በሬ ሽጠው ገንዘቡንና የሞተውን እንስሳ እኩል ይካፈሉ።

36. ሆኖም በሬው የመዋጋት ዐመል ያለው መሆኑ ከታወቀ፣ ባለቤቱም በረት ሳይዘጋበት ቢቀር፣ ባለቤቱ በሬውን በበሬው ፈንታ ይክፈል፤ የሞተውም እንስሳ ለእርሱ ይሆናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 21