ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 20:9-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ስድስት ቀን ትሠራለህ፤ ሥራህንም ሁሉ አከናውን።

10. ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕለቱ አንተም ሆንህ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህ ወይም ሴት አገልጋይህ፣ ወይም እንስሳትህ፣ ወይም በግቢህ ያለ መጻተኛ ምንም ሥራ አትሠሩም።

11. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንና በውስጡም ያሉትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ፤ በሰባተኛው ቀን አርፎአልና። ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰንበትን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም።

12. ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።

13. “አትግደል።

14. “አታመንዝር።

15. “አትስረቅ።

16. “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።

17. “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ።

18. “ሕዝቡም መብረቁንና ነጎድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤

19. ሙሴን፣ “አንተ ራስህ ተናገረን፤ እኛም እናደምጥሃለን፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንዲናገረን አታድርግ፤ አለበለዚያ መሞታችን ነው” አሉት።

20. ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍርሃት ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሊፈትናችሁ መጥቶአል” አላቸው።

21. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 20