ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 20:12-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ (ያህዌ ኤሎሂም) በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።

13. “አትግደል።

14. “አታመንዝር።

15. “አትስረቅ።

16. “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።

17. “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ።

18. “ሕዝቡም መብረቁንና ነጎድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤

19. ሙሴን፣ “አንተ ራስህ ተናገረን፤ እኛም እናደምጥሃለን፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንዲናገረን አታድርግ፤ አለበለዚያ መሞታችን ነው” አሉት።

20. ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍርሃት ከእናንተ ጋር ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሊፈትናችሁ መጥቶአል” አላቸው።

21. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር።

22. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ለእስራኤላውያን ይህን ንገራቸው፤ ‘ከሰማይ ሆኜ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤

23. ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከብር ወይም ከወርቅ ለእናንተ አማልክትን አታብጁ።

24. “ ‘የጭቃ መሠዊያን ሥራልኝ፤ በእርሱም ላይ የሚቃጠልና የኅብረት መሥዋዕትን ከበጎችህ፣ ከፍየሎችህና ከቀንድ ከብቶችህ ሠዋልኝ፤ ስሜ እንዲከበር በማደርግበት ቦታ ሁሉ ወደ አንተ እመጣና እባርክሃለሁ።

25. ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ፣ ከጥርብ ድንጋይ አትሥራ፤ መሣሪያ የነካው ከሆነ ታረክሰዋለህና።

26. ወደ መሠዊያዬም በደረጃ አትውጣ፤ አለዚያ ኀፍረተ ሥጋህ ይገለጣል’።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 20