ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 16:22-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ጎሞር አድርገው እጥፍ ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም አለቆች ወደ ሙሴ መጥተው ይህንኑ ነገሩት።

23. እርሱም አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘ነገ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ የተቀደሰ ሰንበት በመሆን፣ የዕረፍት ቀን ይሆናል። ስለዚህ መጋገር የምትፈልጉትን ጋግሩ፤ መቀቀል የምትፈልጉትን ቀቅሉ። የተረፈውን አስቀምጡ፤ እስከ ጧትም ድረስ አቆዩት።

24. ስለዚህ ሙሴ እንዳዘዘው እስከ ጧት ድረስ አቆዩት፤ አልሸተተም፤ ወይም አልተላም።

25. ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነውና። ዛሬ በመሬት ላይ ምንም አታገኙም።

26. ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም።”

27. ሆኖም አንዳንዶቹ በሰባተኛው ቀን ለመሰብሰብ ወጡ፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም።

28. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን ለመፈጸም እስከ መቼ እምቢ ትላላችሁ?

29. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበትን የሰጣችሁ መሆኑን ልብ በሉ፤ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን እንጀራ የሰጣችሁ ለዚህ ነው። በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ባለበት ይቆይ፤ ማንም አይወጣም።”

30. ስለዚህ ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፉ።

31. የእስራኤልም ሕዝብ ምግቡን መና አሉት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ፣ ጣሙም ከማር እንደ ተጋገረ ቂጣ ነበር።

32. ሙሴም አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘን ይህ ነው፤ ‘ከግብፅ ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ እንድትበሉ የሰጠኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ አንድ ጐሞር መና ወስደህ ለሚመጡት ትውልዶች አቆየው።’ ”

33. ስለዚህ ሙሴ አሮንን፣ “አንድ ማሰሮ ወስደህ አንድ ጎሞር መና አስቀምጥበት፤ ለሚመጡት ትውልዶች እንዲቆይም እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አስቀምጠው” አለው።

34. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው አሮን፣ መናው ይጠበቅ ዘንድ በምስክሩ ፊት አስቀመጠው።

35. እስራኤላውያን ወደ መኖሪያቸው ምድር እስኪመጡ ድረስ ለአርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ድንበር እስከሚደርሱ ድረስ መና በሉ።

36. አንድ ጎሞር የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 16