ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 16:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር።

14. ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ አመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ።

15. እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።ሙሴም፦ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው።

16. እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጐሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዞአል።

17. እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ።

18. የሰበሰቡትን በጐሞር በሰፈሩ ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም ጥቂት የሰበሰበውም አልጐደለበትም እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ።

19. ሙሴም፣ “ማንም ከዚህ ለነገ ምንም ማስተረፍ የለበትም” አላቸው።

20. ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግሥቱም ጠዋት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው።

21. በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ።

22. ስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ጎሞር አድርገው እጥፍ ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም አለቆች ወደ ሙሴ መጥተው ይህንኑ ነገሩት።

23. እርሱም አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘ነገ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ የተቀደሰ ሰንበት በመሆን፣ የዕረፍት ቀን ይሆናል። ስለዚህ መጋገር የምትፈልጉትን ጋግሩ፤ መቀቀል የምትፈልጉትን ቀቅሉ። የተረፈውን አስቀምጡ፤ እስከ ጧትም ድረስ አቆዩት።

24. ስለዚህ ሙሴ እንዳዘዘው እስከ ጧት ድረስ አቆዩት፤ አልሸተተም፤ ወይም አልተላም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 16