ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 14:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በከበርሁ ጊዜ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደሆንሁ ያውቃሉ።

19. ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዓምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤

20. በግብፅና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም።

21. ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃው ተከፈለ፤

22. እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ አለፉ።

23. ግብፃውያንም አሳደዷቸው፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ ሰረገሎችና ፈረሰኞች በሙሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ ገቡ።

24. ሲነጋጋም እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሰራዊት ቍልቍል ተመለከተ፤ በግብፃውያን ሰራዊት ላይም ሽብር ላከባቸው።

25. መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው ግብፃውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር (ያህዌ) ግብፅን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ።

26. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ውሃው ግብፃውያንን ሠረገሎቻቸውንና ፈረሰኞቻቸውን ተመልሶ እንዲሸፍናቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ” አለው።

27. ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ንጋት ላይም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ። ግብፃውያን ከውሃው ሸሹ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ግብፃውያንን በባሕሩ ውስጥ ጣላቸው።

28. ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው ወደ ባሕሩ የገቡትን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞች፣ መላውን የግብፅ ሰራዊት ሁሉ ሸፈነ። አንድም እንኳ አልተረፈም።

29. እስራኤላውያን ግን ውሃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ፣ በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ።

30. በዚያች ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) እስራኤልን ከግብፃውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም የግብፃውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ወድቆ ተመለከቱ።

31. እስራኤላውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና (ያህዌ)፣ በባሪያው በሙሴም አመኑ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 14