ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 12:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ወሩ በገባ እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቋቸው። በዚያ ምሽት ጀምበር ስትጠልቅ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይረዷቸው።

7. ከዚያም ከደሙ ወስደው የጠቦቶቹ ሥጋ የሚበላበትን የእያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃንና ጉበን ይቀቡ።

8. ሥጋውንም በዚያችው ሌሊት በእሳት ላይ ጠብሰው ከመራራ ቅጠልና ካልቦካ ቂጣ ጋር ይብሉት።

9. ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን፣ እግሮቹንና ሆድ ዕቃውን በእሳት ላይ ጠብሳችሁ ብሉት።

10. ከሥጋው ተርፎ አይደር፤ ያደረ ቢኖር ግን በእሳት ይቃጠል።

11. ስትበሉም ልብሳችሁን ለብሳችሁ፣ ባጭር ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁ በትራችሁን ይዛችሁ በጥድፊያ ብሉት፤ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ ነው።

12. “እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ ምድር ላይ አልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብፅን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

13. ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን አልፋለሁ፤ ግብፅን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም።

14. “ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ።

15. ለሰባት ቀናት እርሾ የሌለበትን ቂጣ ብሉ፤ በመጀመሪያው ቀን እርሾን ሁሉ ከቤታችሁ አስወግዱ፤ በነዚህ ሰባት ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል ይወገድ።

16. በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባዔ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ፤ የምትሠሩት ሥራ ቢኖር ለእያንዳንዱ ምግብ ማዘጋጀት ብቻ ይሆናል።

17. የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ሰራዊታችሁን ከግብፅ ምድር ያወጣሁት በዚች ዕለት ነውና። ይህን ዕለት ለሚቀጥለው ትውልድ ቋሚ ሥርዐት በማድረግ አክብሩት።

18. ከመጀመሪያው ወር ከአሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ሃያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ እርሾ የሌለበት ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ።

19. ለሰባት ቀን እርሾ በቤታችሁ አይኑር፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ከእስራኤል ማኅበር ይወገድ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 12