ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 12:39-50 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

39. ከግብፅ ይዘው ከወጡት ሊጥ ያልቦካ ቂጣ ጋገሩ፤ ሊጡ አልቦካም ነበር፤ ምክንያቱም ከግብፅ በጥድፊያ እንዲወጡ ስለተደረጉ፣ ለራሳቸው ምግብ ለማዘጋጀት ጊዜ አልነበራቸውም።

40. እንግዲህ እስራኤላውያን በግብፅ የኖሩበት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነበር።

41. ልክ አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመ ዕለት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰራዊት ሁሉ ግብፅን ለቆ ወጣ።

42. እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚያች ሌሊት እነርሱን ከግብፅ ለማውጣት ዘብ የቆመበት በመሆኑ፣ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ያከብሩ ዘንድ፣ በዚያች ሌሊት እስራኤላውያን ሁሉ ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል።

43. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “የፋሲካ በዓል አከባበር ሥርዐት እንዲህ ነው፤ ባዕድ የሆነ ሰው ከፋሲካው ምግብ አይብላ፤

44. በገንዘብ የገዛኸው ማንኛውም ባሪያ ከገረዝኸው በኋላ መብላት ይችላል፣

45. ነገር ግን ለጊዜው የተቀመጠ እንግዳና ቅጥር ሠራተኛ መብላት የለበትም።

46. “ምግቡ በአንድ ቤት ውስጥ መበላት አለበት፤ ምንም ሥጋ ከቤት እንዳይወጣ፤ ምንም አጥንት እንዳትሰብሩ።

47. የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በዓሉን ማክበር ይኖርበታል።

48. “በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የፋሲካ በዓል ማክበር ቢፈልግ፣ በቤተ ሰቡ ያሉት ወንዶች ሁሉ መገረዝ አለባቸው፤ ከዚያም እንደ ተወላጅ ተቈጥሮ የሥርዐቱ ተካፋይ ይሁን። ያልተገረዘ ወንድ ግን የፋሲካን ምግብ አይብላ።

49. ይህም ሕግ በዜጋውም ሆነ በመካከላችሁ በሚኖሩት መጻተኞች ላይ እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።”

50. እስራኤላውያን በሙሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን ያዘዘውን ሁሉ ፈጸሙ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 12