ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 8:7-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ጅረቶችና የኵሬ ውሃ ወዳለበት፣ ምንጮች ከየሸለቆውና ከየኰረብታው ወደሚፈሱበት ወደ መልካሚቱ ምድር ያገባል፤

8. ስንዴና ገብስ፣ ወይንና የበለስ ዛፎች፣ ሮማን፣ የወይራ ዘይትና ማር የሚገኝባት ምድር፤

9. ምንም ነገር የማይታጣባት፣ የዳቦም ዕጦት የሌለባት፣ ዐለቶች ብረት የሆኑባት፣ ከኰረብቶቿም መዳብ ቈፍረህ ልታወጣ የምትችልባት ምድር ናት።

10. በልተህ በምትጠግብበት ጊዜ እንዲህ ያለች መልካም ምድር ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ባርከው።

11. በዛሬዪቱ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሕጉንና ሥርዐቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንዳትረሳው ተጠንቀቅ።

12. አለበለዚያ በልተህ ስትጠግብና ጥሩ ጥሩ ቤቶችን ሠርተህ መኖር ስትጀምር፣

13. ደግሞም የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህ ሲበዛ፣ ብርህና ወርቅህ ሲበረክት፣ ያለህም ሁሉ በላይ በላዩ እየጨመረ ሲሄድ፣

14. ልብህ ይታበይና ከባርነት ምድር፣ ከግብፅ ያወጣህን አምላክህንእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትረሳለህ።

15. በዚያ ጭልጥ ባለና አስፈሪ ምድረ በዳ፣ በዚያ በሚያስጠማና ውሃ በማይገኝበት ደረቅ መሬት፣ መርዘኛ እባብና ጊንጥ ባለበት ምድረ በዳ መራህ፤ ከጽኑ ዐለትም ውሃ አፈለቀልህ።

16. በመጨረሻ መልካም እንዲሆንልህ፣ አንተን ትሑት ለማድረግና ለመፈተን፣ አባቶችህ ፈጽሞ የማያውቁትን መና በምድረ በዳ መገበህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 8