ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 7:13-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ይወድሃል፤ ይባርክሃል፤ ያበዛሃልም። ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የማሕፀንህን ፍሬ፣ የምድርህን ሰብል፣ እህልህን፣ አዲሱን ወይንና ዘይት፤ የከብት መንጋህን ጥጆች፣ የበግና የፍየል መንጋህን ግልገሎች ይባርካል።

14. ከሕዝቦች ሁሉ የበለጠ አንተ ትባረካለህ፤ ከአንተ ወይም ከከብቶችህ መካከል የማይወልድ ወንድ ወይም ሴት አይኖርም።

15. እግዚአብሔር (ያህዌ) ከማናቸውም በሽታ ነጻ ያደርግሃል፤ በግብፅ የምታውቃቸውን እነዚያን አሠቃቂ በሽታዎች በሚጠሉህ ሁሉ ላይ እንጂ በአንተ ላይ አያመጣብህም።

16. አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ማጥፋት አለብህ፤ አትዘንላቸው፤ ወጥመድ ስለሚሆኑብህም አማልክታቸውን አታምልክ።

17. “እነዚህ አሕዛብ ከእኛ ይልቅ ጠንካሮች ስለሆኑ፣ እንዴት አድርገን እናስወጣቸዋለን?” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል።

18. ነገር ግን አትፍራቸው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በፈርዖንና በግብፅ ሁሉ ላይ ያደረገውን በሚገባ አስታውስ።

19. ታላላቅ ፈተናዎችን፣ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አንተን ያወጣበትን ብርቱ እጅና የተዘረጋች ክንድ በገዛ ዐይንህ አይተሃል። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አሁን በምትፈራቸው ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያንኑ ያደርጋል።

20. ይልቁንም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሕይወት ተርፈው፣ ከአንተ የተደበቁት እንኳ እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ተርብ ይሰድባቸዋል።

21. በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ (ኤሎሂም) ስለ ሆነ አያስደንግጡህ።

22. አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት ከፊትህ ያስወጣቸዋል፤ የዱር አራዊቱ ቊጥር በአካባቢህ እንዳይበራከት ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማጥፋት አይፈቀድልህም፤

23. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ግን እስኪጠፉ ድረስ ከባድ ትርምስ ፈጥሮባቸው በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 7