ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 4:22-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. እኔም በዚህች ምድር እሞታለሁ፤ ዮርዳኖስን አልሻገርም፤ እናንተ ግን ልትሻገሩ ነው፤ ያችንም መልካም ምድር ትወርሳላችሁ።

23. አምላካችሁእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባውን ኪዳን እንዳትረሱ ተጠንቀቁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የከለከለውን ጣዖት በማናቸውም ዐይነት መልክ ለራሳችሁ አታብጁ።

24. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚባላ እሳት ቀናተኛም አምላክ (ኤሎሂም) ነውና።

25. ልጆችንና የልጅ ልጆችን ከወለዳችሁና በምድሪቱም ላይ ለረጅም ጊዜ ከኖራችሁ በኋላ ራሳችሁን በማርከስ ማንኛውንም ዐይነት ጣዖት ብታበጁ፣ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ክፋት በማድረግ ለቊጣ ብታነሣሡት፣

26. ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትወርሷት ምድር ላይ ፈጥናችሁ እንደምትጠፉ በዚህ ቀን ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ምስክሮች አድርጌ እጠራለሁ፣ በዚያ ቦታ ብዙ ዘመን አትኖሩም፤ ፈጽሞ ትጠፋላችሁ።

27. እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፤ እግዚአብሔር በሚበትናችሁ አሕዛብ መካከል የምትተርፉት ጥቂቶቻችሁ ብቻ ናችሁ።

28. እዚያም፣ ማየት ወይም መስማት ወይም መብላት ወይም ማሽተት በማይችሉ በሰው እጅ በተሠሩ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካላችሁ።

29. ነገር ግን እዚያም ሆናችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ብትፈልጉት ታገኙታላችሁ።

30. ስትጨነቅና ይህ ሁሉ ነገር ሲደርስብህ ያን ጊዜ፣ በኋለኞቹ ዘመናት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትመለሳለህ፤ ትታዘዝለታለህም።

31. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሓሪ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና፣ አይተውህም ወይም አያጠፋህም፤ ወይም ደግሞ ለአባቶችህ በመሐላ ያጸናላቸውን ቃል ኪዳን አይረሳም።

32. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረበት ቀን ጀምሮ እናንተ ከመኖራችሁ በፊት ስለ ነበረው የቀድሞ ዘመን ጠይቁ፤ ከአንዱ የሰማይ ጫፍ እስከ ሌላው የሰማይ ጫፍ ድረስ ጠይቅ፤ እንደዚህ ያለ ታላቅ ነገር ከቶ ተደርጎ ወይስ እንደዚህ ዐይነት ነገር ከቶ ተሰምቶ ያውቃልን?

33. ከእሳት ውስጥ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ድምፅ እንደ እናንተ የሰማና በሕይወት የኖረ ከቶ ሌላ ሕዝብ አለን?

34. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች ከሌላ ሕዝብ መካከል አንድን ሕዝብ የራሱ ለማድረግ የቻለ አምላክ አለን?

35. እግዚአብሔር እርሱ አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኑን፣ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን ታውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እንድታዩ ተደረገ።

36. ሊገሥጽህ ድምፁን ከሰማይ እንድትሰማ አደረገ፤ በምድርም ላይ አስፈሪ እሳቱን አሳየህ፤ ከእሳቱም ውስጥ ቃሉን ሰማህ።

37. አባቶችህን ከመውደዱ የተነሣና ከእነርሱም በኋላ ዘራቸውን ስለ መረጠ፣ ከአንተ ጋር በመሆን በታላቅ ኀይሉ ከግብፅ አወጣህ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 4