ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 4:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አሁንም እስራኤል ሆይ፤ በሕይወት እንድትኖሩ፣ የአባቶቻችሁ አምላክእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጣችሁ ምድር እንድትገቡና እንድትወርሱ የማስተምራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ ጠብቋቸውም።

2. ባዘዝኋችሁ ላይ አትጨምሩ፤ ከእርሱም አትቀንሱ፤ ነገር ግን የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች ጠብቁ።

3. እግዚአብሔር (ያህዌ) በብዔልፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከመካከላችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቶአቸዋል፤

4. አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት አላችሁ።

5. ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ (ያህዌ ኤሎሂም) ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ።

6. በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ “በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው” ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 4