ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 32:4-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም (ኤሎሂም) እርሱ ነው።

5. በእርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም፤ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው።

6. አንተ ተላላና ጥበብ የጐደለህ ሕዝብ፣ ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) የምትመልስለት በዚህ መንገድ ነውን?አባትህ ፈጣሪህ፣የሠራህና ያበጀህ እርሱ አይደለምን?

7. የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርሃልም፤ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ያስረዱሃል።

8. ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን በሰጠ ጊዜ፣የሰውንም ዘር በለያየ ጊዜ፣በእስራኤል ልጆች ቊጥር ልክ፣የአሕዛብን ርስት ድንበር ለየ፤

9. የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የገዛ ሕዝቡ፣ያዕቆብ የተለየ ርስቱ ነውና።

10. እርሱን በምድረ በዳ፣ባዶና ጭው ባለ በረሓ ውስጥ አገኘው፤ጋሻ ሆነው፤ ተጠነቀቀለትም፤እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቀው።

11. ንስር ጎጆዋን በትና፣በጫጩቶቿም ላይ እንደምትረብብ፣እነርሱን ለመያዝ ክንፎቿን እንደምትዘረጋ፣በክንፎቿም እንደምትሸከማቸው፣

12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ብቻ መራው፤ምንም ባዕድ አምላክ አብሮት አልነበረም።

13. በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤የዕርሻንም ፍሬ መገበው፤ከዐለት ድንጋይ ማር አበላው፤ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው።

14. የላሙንና የበጉን መንጋ ቅቤና ወተት፣የሰቡትን በጎችና ፍየሎች፣የባሳንን ምርጥ አውራ በግ፣መልካም የሆነውንም ስንዴ፣ማለፊያውንም የወይን ጠጅ፣

15. ይሹሩን ወፈረ፤ ረገጠ፤ጠገበ፤ ሰውነቱ ደነደነ፤ ለሰለሰ፤የፈጠረውንም አምላክ (ኤሎሂም) ተወ፤መጠጊያ ዐለት የሆነውን አዳኙንም ናቀ።

16. በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፤በአስጸያፊ ጣዖቶቻቸውም አስቈጡት።

17. አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፦ላላወቋቸው አማልክት፣ከጊዜ በኋላ ለተነሡ አማልክት፣አባቶቻችሁ ላልፈሯቸው አማልክት ሠዉ።

18. አባት የሆነህን ዐለት ከዳኸው፤የወለደህን አምላክ (ኤሎሂም) ረሳኸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 32