ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 31:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።”

7. ከዚያም ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻቸው ሊሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋር አብረህ ስለምትገባ፣ ምድሪቱን ርስታቸው አድርገህ ስለምታከፋፍል በርታ፤ ደፋርም ሁን።

8. እግዚአብሔር (ያህዌ) ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።”

9. ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙ ለሌዊ ልጆች፣ ለካህናቱና ለእስራኤል አለቆች ሁሉ ሰጠ።

10. ከዚያም በኋላ ሙሴ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዕዳ በሚተውበት፣ የዳስ በዓልም በሚከበርበት፣ በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፣

11. እስራኤል ሁሉ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህበእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ሲታይ ይህን ሕግ በእነርሱ ፊት በጆሮአቸው ታነበዋለህ።

12. ይሰሙና አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ።

13. ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሷት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።

14. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እነሆ የምትሞትበት ቀን ቀርቦአል፤ ትእዛዝ እንድሰጠው ኢያሱን ጥራውና ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ።” ሙሴና ኢያሱም ሄዱ፤ ወደ መገናኛው ድንኳንም ቀረቡ።

15. እግዚአብሔርም (ያህዌ) በድንኳኑ ላይ በደመና ዐምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዐምድ ከድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ።

16. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፣ ከአባቶችህ ጋር ልታርፍ ነው፤ ይህም ሕዝብ በሚገባበት ምድር በሚገኙ ባዕዳን አማልክት ወዲያውኑ ያመነዝራል። እኔን ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳሉ።

17. በዚያች ቀን እቈጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፣ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፣ አምላካችን (ኤሎሂም) ከእኛ ጋር ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ።

18. ወደ ባዕዳን አማልክት በመዞር ከፈጸሙት ክፋታቸው የተነሣ፣ በዚያች ቀን ፊቴን ከእነርሱ ፈጽሞ እሰውራለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 31