ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 31:3-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ራሱ በፊትህ ቀድሞ ይሄዳል፤ እነዚህንም አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ አንተም ምድራቸውን ትወርሳለህ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው፣ ኢያሱም አንተን ቀድሞ ይሻገራል።

4. እግዚአብሔር (ያህዌ) የአሞራውያንን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን ከነምድራቸው እንዳጠፋቸው እነዚህንም ያጠፋቸዋል።

5. እግዚአብሔር (ያህዌ) እነርሱን በፊታችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ያዘዝኋችሁን ሁሉ በእነርሱ ላይ ታደርጋላችሁ።

6. ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።”

7. ከዚያም ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻቸው ሊሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋር አብረህ ስለምትገባ፣ ምድሪቱን ርስታቸው አድርገህ ስለምታከፋፍል በርታ፤ ደፋርም ሁን።

8. እግዚአብሔር (ያህዌ) ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።”

9. ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙ ለሌዊ ልጆች፣ ለካህናቱና ለእስራኤል አለቆች ሁሉ ሰጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 31