ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 31:17-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. በዚያች ቀን እቈጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፣ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፣ አምላካችን (ኤሎሂም) ከእኛ ጋር ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ።

18. ወደ ባዕዳን አማልክት በመዞር ከፈጸሙት ክፋታቸው የተነሣ፣ በዚያች ቀን ፊቴን ከእነርሱ ፈጽሞ እሰውራለሁ።

19. “እንግዲህ ይህን መዝሙር ለራሳችሁ ጻፉ፤ ለእስራኤል ልጆችም አስተምሩ፤ ስለ እኔ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ እንዲዘምሩ አድርጉ።

20. ወተትና ማር ወደምታፈሰውና ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ባመጣኋቸው ጊዜ ከበሉና ከጠገቡ፣ ከበለጸጉም በኋላ እኔን ንቀው ኪዳኔንም አፍርሰው ወደ ባዕዳን አማልክት ይዞራሉ፤ እነርሱንም ያመልካሉ።

21. ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር በደረሰባቸው ጊዜ ይህ መዝሙር ምስክር ይሆንባቸዋል። በዘራቸው የሚረሳ አይደለምና። ወደማልሁላቸው ምድር ሳላስገባቸው በፊት ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ እንኳን አስቀድሜ ዐውቃለሁ።”

22. ስለዚህም ሙሴ ይህን መዝሙር በዚያች ቀን ጻፈ፤ ለእስራኤላውያንም አስተማራቸው።

23. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለነዌ ልጅ ለኢያሱ፣ “በርታ፤ ደፋር ሁን፤ የእስራኤልን ልጆች በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ታስገባቸዋለህና፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት ትእዛዝ ሰጠው።

24. ሙሴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የዚህን ሕግ ቃል በመጽሐፍ ጽፎ እንዳበቃ፣

25. የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የኪዳን ታቦት የሚሸከሙ ሌዋውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤

26. “ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፤ በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖር ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የኪዳን ታቦት አጠገብ አስቀምጡት፤ ይህም በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖራል፤

27. የቱን ያህል ዐመፀኞችና ዐንገተ ደንዳኖች እንደሆናችሁ ዐውቃለሁና። እኔ በሕይወት ከእናንተ ጋር እያለሁ እንደዚህ ካመፃችሁ፣ ከሞትሁ በኋላማ የቱን ያህል ልታምፁ

28. ይህን ቃል ይሰሙ ዘንድ እንድናገር፣ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እንድጠራባቸው፣ የነገድ አለቆቻችሁን በሙሉና ሹሞቻችሁን ሁሉ በፊቴ ሰብስቡ።

29. እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንደምትረክሱ፣ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ ዐውቃለሁና። በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ክፉ ድርጊት ስለምትፈጽሙ፣ እጆቻችሁ በሠሯቸውም ነገሮች እርሱን ለቊጣ ስለምታነሣሡት፣ በሚመጡት ዘመናት ጥፋት ይደርስባችኋል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 31