ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 30:9-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ከዚያም አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ ሥራ ሁሉና በወገብህ ፍሬ፣ በእንስሳትህ ግልገሎችና በምድርህ ሰብል እጅግ ያበለጽግሃል። በአባቶችህ ደስ እንደ ተሰኘ ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋልና።

10. ይህም የሚሆነው፣ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ከታዘዝህና በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዐቱን በመጠበቅ፣ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስትመለስ ነው።

11. በዛሬው ዕለት የምሰጥህ ትእዛዝ ይህን ያህል አስቸጋሪ ወይም ከአንተ የራቀች አይደለችም።

12. “እንድንፈጽማት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ፣ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?” እንዳትል፣ በላይ በሰማይ አይደለችም።

13. ደግሞም፣ “እንድናደርጋት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ፣ ማን ባሕሩን ይሻገራል?” እንዳትልም፣ ከባሕር ማዶ አይደለችም።

14. ነገር ግን ቃሉ ለአንተ በጣም ቅርብ ነው፤ ታደርገውም ዘንድ በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው።

15. እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትንና በረከትን፣ ሞትንና ጥፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ።

16. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትወድ፣ በመንገዱም እንድትሄድና ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን እንድትጠብቅ አዝሃለሁ፤ ከዚያም በሕይወት ትኖራለህ፤ ትበዛለህም፤ አምላክህም እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትወርሳት ዘንድ በምትገባበት ምድር ይባርክሃል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 30