ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የባሳን ንጉሥ የዐግ መሸነፍ

1. ከዚያም፣ ተመልሰን የባሳንን መንገድ ይዘን ወጣን፤ የባሳን ንጉሥ ዐግም ከመላው ሰራዊቱ ጋር ሆኖ በኤድራይ ጦርነት ሊገጥመን ተነሣ።

2. እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “እርሱን፣ መላው ሰራዊቱንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ስለ ሰጠሁህ፣ አትፍራው፤ ሐሴቦንን ይገዛ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ ያደረግህበትን በእርሱም ላይ አድርግበት” አለኝ።

3. ስለዚህ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የባሳንን ንጉሥ ዐግንና ሰራዊቱን ሁሉ እንደዚሁ በእጃችን ላይ ጣላቸው፤ እኛም አንድ እንኳ በሕይወት ሳናስቀር አጠፋናቸው።

4. በዚያን ጊዜ ከተሞቹን ሁሉ ያዝን፤ የዐግ ግዛት ከሆነው፣ በባሳን ከሚገኘው ከጠቅላላው የአርጎብ ክልል ሥልሳ ከተሞች ውስጥ፣ እኛ ያልያዝነው አንድም ከተማ አልነበረም።

5. እነዚህ ከተሞች ሁሉ ከፍ ባሉ ቅጥሮች፣ በመዝጊያዎችና በመወር ወሪያዎች የተመሸጉ ነበሩ፤ እንዲሁም ቅጥር የሌላቸው አያሌ መንደሮች ነበሩ።

6. በእያንዳንዱ ከተማ ያሉትን ወንዶቹን፣ ሴቶቹንና ልጆቻቸውን ጭምር በማጥፋት፣ በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግነው ሁሉ፣ እነዚህንም ፈጽመን ደመሰስናቸው።

7. ከብቱን በሙሉና ከየከተሞቻቸው የማረክነውን ሁሉ ግን ለራሳችን አደረግን።

8. ስለዚህ በዚያን ጊዜ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን፣ ከአርኖን ሸለቆ እስከ አርሞንዔም ተራራ ያለውን ግዛት፣ ከእነዚህ ከሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ላይ ወሰድንባቸው።

9. አርሞንዔምን፣ ሲዶናውያን ሢርዮን ብለው ሲጠሩት፣ አሞራውያን ግን ሳኔር ይሉታል።

10. በከፍታው ቦታ ላይ የሚገኙትን ከተሞች በሙሉ፣ ገለዓድን እንዳለ፣ እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ያለውን ባሳንን ሁሉ እንዲሁም በባሳን ውስጥ የሚገኙትን የዐግ ግዛት ከተሞች በእጃችን አደረግን።

11. ከራፋይማውያን ወገን የተረፈ የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻ ነበር። ዐልጋው ከብረት የተሠራ ቁመቱም ዘጠኝ ክንድ፣ ስፋቱ ደግሞ አራት ክንድ ነበር። ይህም እስካሁን በአሞናውያን ከተማ በረባት ይገኛል።

እስራኤላውያን ምድሪቱን መከፋፈላቸው

12. በዚያን ጊዜ ከያዝነው ምድር ላይ በአርኖን ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር አንሥቶ በስተ ሰሜን ያለውን ግዛት፣ በተጨማሪም ኰረብታማውን የገለዓድ አገር እኩሌታ ከነከተሞቹ ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው።

13. ቀሪውን የገለዓድ ምድርና የዐግ ግዛት የሆነውን ባሳንን በሙሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ። በባሳን የሚገኘው መላው የአርጎብ ክልል የራፋይማውያን ምድር በመባል ይታወቅ ነበር።

14. ከምናሴ ነገድ የሆነው ኢያዕር፣ እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ወሰን ድረስ የሚገኘውን መላውን የአርጎብ ምድር ወሰደ፤ ምድሪቱም በስሙ ተጠራች፤ ከዚሁ የተነሣ ባሳን እስከ ዛሬ ድረስ ሓቦት ኢያዕር ትባላለች።

15. ገለዓድንም ለማኪር ሰጠሁት።

16. ነገር ግን የሸለቆውን እኩሌታ ወሰን በማድረግ ከገለዓድ አንሥቶ እስከ አርኖን ሸለቆ፣ ከዚያም የአሞናውያን ድንበር እስከ ሆነው እስከ ያቦቅ ወንዝ ያለውን ግዛት ለሮቤላውያንና ለጋዳውያን ሰጠኋቸው።

17. የምዕራቡ ወሰን፣ በዓረባ የሚገኘው ዮርዳኖስ ሲሆን፣ ይኸውም ከፈስጋ ተረተሮች በታች፣ ከኪኔሬት አንሥቶ የጨው ባሕር እስከሚባለው እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ ነው።

18. በዚያን ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ለእናንተ ሰጥቶአችኋል፤ ይሁን እንጂ የአካል ብቃት ያላቸው ሰዎቻችሁ ሁሉ ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ፊት በመቅደም መሻገር አለባቸው።

19. ሆኖም ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ፣ (ብዙ ከብቶች እንዳሏችሁም ስለማውቅ) ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ውስጥ ይቈዩ፤

20. ይኸውም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእናንተ እንዳደረገው ሁሉ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፋቸውና አምላካችሁእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዮርዳኖስ ማዶ የሚሰጣቸውን ምድር እነርሱም እንደዚሁ እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያ በኋላ እያንዳንዳችሁ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ።”

ሙሴ ዮርዳኖስን እንዳይሻገር መከልከሉ

21. በዚያን ጊዜ ኢያሱን እንዲህ ስል አዘዝሁት፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእነዚህ በሁለቱ ነገሥታት ላይ ያደረገውን ሁሉ በገዛ ዓይንህ አይተሃል፤ አሁንም ዐልፈህ በምትሄድባቸው መንግሥታት ላይ ሁሉ እግዚአብሔር ይህንኑ ይደግመዋል።

22. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ራሱ ይዋጋላችኋልና አትፍሯቸው።”

23. በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ ብዬ ለመንሁት፤

24. “ጌታ እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ሆይ፣ ታላቅነትህንና ብርቱ ክንድህን ለእኔ ለባሪያህ እነሆ ማሳየት ጀምረሃል፤ ለመሆኑ በሰማይም ሆነ በምድር፣ አንተ የምታደርጋቸውን ሥራዎችና ታላላቅ ድርጊቶች መፈጸም የሚችል አምላክ ማነው?

25. አሁንም ከዮርዳኖስ ማዶ ያለችውንያችን መልካሚቱን ምድር፣ ውብ የሆነችውን ኰረብታማ አገርና ሊባኖስን እንዳይ ፍቀድልኝ።”

26. እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን በእናንተ ሰበብ ተቈጥቶኝ ነበርና አልሰማኝም፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “ይበቃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ስለዚህ ነገር አታንሣብኝ።

27. ወደ ፈስጋ ተራራ ጫፍ ውጣ፤ ወደ ምዕራብና ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅም ተመልከት። አንተ ዮርዳኖስን ስለማትሻገር፣ ምድሪቱን በዐይንህ ብቻ እያት።

28. ነገር ግን ሕዝቡን መርቶ በማሻገር የምታያትን ምድር እንዲወርሱ የሚያደርጋቸው ስለ ሆነ፣ ኢያሱን ላከው፤ አደፋፍረው፤ አበረታታውም።”

29. ስለዚህ እኛ በቤተ ፌጎር አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ ቈየን።