ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 28:9-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፣ በመሐላ በሰጠህ ተስፋ መሠረት የተቀደሰ ሕዝቡ አድርጎ ያቆምሃል፤

10. ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም።

11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል።

12. እግዚአብሔር (ያህዌ) ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም።

13. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህንየእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ መቼውንም ቢሆን እላይ እንጂ ፈጽሞ እታች አትሆንም።

14. ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል።

15. ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፣ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀ ልቁሃልም፦

16. በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ።

17. እንቅብህና ቡሓቃህ የተረገሙ ይሆናሉ።

18. የማሕፀንህ ፍሬ፣ የዕርሻህ ሰብል፣ የመንጋህ ጥጆች፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህ ይረገማሉ።

19. ስትገባ ትረገማለህ፤ ስትወጣም ትረገማለህ።

20. እርሱን በመተው ክፉ ድርጊት ከመፈጸምህ የተነሣ፣ እስክትደመሰስ ፈጥነህም እስክትጠፋ ድረስ እጅህ በነካው ሁሉ ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) ርግማንን፣ መደናገርንና ተግሣጽን ይሰድብሃል።

21. እግዚአብሔር (ያህዌ) ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ላይ እስኪ ያጠፋህ ድረስም፣ በደዌ ይቀሥፍሃል።

22. እግዚአብሔር (ያህዌ) እስክትጠፋ ድረስ በሚቀሥፍ ደዌ፣ ትኵሳትና ዕባጭ፣ ኀይለኛ ሙቀትና ድርቅ፣ ዋግና አረማሞ ይመታሃል።

23. ከራስህ በላይ ያለው ሰማይ ናስ፣ ከእግርህ በታች ያለው ምድርም ብረት ይሆናል።

24. እግዚአብሔር (ያህዌ) የምድርህን ዝናብ ወደ ዐቧራነትና ወደ ትቢያነት ይለውጠዋል፤ ይህም እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።

25. እግዚአብሔር (ያህዌ) በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ ለምድር መንግሥታትም ሁሉ መሸማቀቂያ ትሆናለህ።

26. ሬሳህ የሰማይ አሞሮችና የምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ በማስፈራራትም የሚያባርራቸው አይኖርም።

27. እግዚአብሔር (ያህዌ) በማትድንበት በግብፅ ብጉንጅ፣ በእባጭ፣ በሚመግል ቊስልና በዕከክ ያሠቃይሃል።

28. እግዚአብሔር (ያህዌ) በእብደት በዕውርነትና ግራ በማጋባት ያስጨንቅሃል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 28