ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 28:24-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. እግዚአብሔር (ያህዌ) የምድርህን ዝናብ ወደ ዐቧራነትና ወደ ትቢያነት ይለውጠዋል፤ ይህም እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።

25. እግዚአብሔር (ያህዌ) በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ ለምድር መንግሥታትም ሁሉ መሸማቀቂያ ትሆናለህ።

26. ሬሳህ የሰማይ አሞሮችና የምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ በማስፈራራትም የሚያባርራቸው አይኖርም።

27. እግዚአብሔር (ያህዌ) በማትድንበት በግብፅ ብጉንጅ፣ በእባጭ፣ በሚመግል ቊስልና በዕከክ ያሠቃይሃል።

28. እግዚአብሔር (ያህዌ) በእብደት በዕውርነትና ግራ በማጋባት ያስጨንቅሃል።

29. በእኩለ ቀን፣ በጨለማ እንዳለ ዕውር በዳበሳ ትሄዳለህ። የምታደርገው ሁሉ አይሳካልህም። በየዕለቱ ትጨቈናለህ፤ ትመዘበራለህም፤ የሚታደግህ አይኖርም።

30. ሚስት ለማግባት ልጃገረድ ታጫለህ፤ ሌላው ግን ወስዶ ይደፍራታል። ቤት ትሠራለህ፣ ግን አትኖርበትም። ወይን ትተክላለህ፤ ፍሬውን ግን አትበላም።

31. በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ከሥጋውም አንዳች አትቀምስም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚያስጥላቸውም አይኖርም።

32. ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕድ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ እጅህንም ለማንሣት ዐቅም ታጣለህ፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ፤ በማለትም ዐይኖችህ ሁል ጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 28