ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ፣ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፣ የፍቺ ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት።

2. ከቤቱ ከወጣች በኋላ ሌላ ባል ብታገባ፣

3. ሁለተኛ ባሏም እንደዚሁ ጠልቷት የፍቺ ወረቀት በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ቢሰዳት ወይም ቢሞት፣

4. ከዚያ በኋላ የፈታት የመጀመሪያ ባሏ፣ የረከሰች በመሆኗ እንደ ገና መልሶ ሊያገባት አይችልም፤ ይህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አስጸያፊ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ኀጢአት አታምጣ።

5. አዲስ ሚስት በቅርብ ጊዜ ያገባ ሰው፣ ለጦርነት አይሂድ፤ ወይም ሌላ ሥራ እንዲሠራ አይገደድ። ለአንድ ዓመት ነጻ ሆኖ እቤቱ ይቈይ፤ ያገባትን ሚስቱን ደስ ያሰኛት።

6. ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም እንኳ ቢሆን፣ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ፤ የሰውን ነፍስ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆናልና።

7. አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፣ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።

8. የለምጽ ደዌን በተመለከተ ሌዋውያን ካህናት የሚሰጡህን መመሪያ በትክክል ለመፈጸም ጥንቃቄ አድርግ። እኔ ለእነርሱ የሰጠሁትን ትእዛዝ በጥንቃቄ ተከተል።

9. ከግብፅ ከወጣችሁ በኋላ በመንገድ ላይ ሳላችሁ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በማርያም ላይ ያደረገባትን አስታውሱ።

10. ማናቸውንም ነገር ለባልንጀራህ ስታበድር መያዣ አድርጎ የሚሰጥህን ለመቀበል ወደ ቤቱ አትግባ።

11. አንተ ከውጭ ሆነህ ጠብቅ፤ ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ከቤት ያምጣልህ።

12. ሰውየው ድኻ ከሆነ፣ መያዣውን ከአንተ ዘንድ አታሳድርበት።

13. መደረቢያውን ለብሶት እንዲያድር ፀሓይ ሳትጠልቅ መልስለት። ከዚያም ያመሰግንሃል፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊትም የጽድቅ ሥራ ሆኖ ይቈጠርልሃል።

14. ድኻና ችግረኛ የሆነውን የምንዳ ሠራተኛ እስራኤላዊ ወንድምህም ሆነ፣ ከከተሞችህ ባንዲቱ የሚኖረውን መጻተኛ አትበዝብዘው፤

15. የሠራበትን ሒሳብ በዕለቱ፣ ፀሓይ ሳትጠልቅ ክፈለው፤ ድኻ በመሆኑ በጒጒት ይጠባበቀዋልና። ያለበለዚያ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ይጮኽና ኀጢአት ይሆንብሃል።

16. አባቶች ስለ ልጆቻቸው፣ ልጆችም ስለ አባቶቻቸው አይገደሉ፤ እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል።

17. ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ።

18. አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዚያ እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው።

19. የዕርሻህን ሰብል በምታጭድበት ጊዜ፣ ተረስቶ የቀረ ነዶ ቢኖር፣ ያን ለመውሰድ ተመልሰህ አትሂድ። አምላክህእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነዶውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው።

20. የወይራ ዛፍህን ፍሬ በምታራግፍበት ጊዜ በየቅርንጫፉ ላይ የቀረውን ለመቃረም ተመልሰህ አትሂድ፤ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው።

21. የወይን ተክልህን ፍሬ ስትሰበስብ ቃርሚያውን ለመሰብሰብ አትመለስበት፤ የቀረውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው።

22. በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው።