ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 2:15-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ከሰፈር ፈጽሞ እስኪያጠፋቸውም ድረስ የእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ በእነርሱ ላይ ነበር።

16. በሕዝቡ መካከል የነበሩት የመጨረሻዎቹ ተዋጊዎች ከሞቱ በኋላ፣

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤

18. “የሞዓብ ዳርቻ ዔርን ዛሬውኑ ታልፋላችሁ።

19. ከየትኛውም የአሞናውያን ምድር ለእናንተ ርስት ስለማልሰጣችሁ፣ አሞናውያን ዘንድ በደረሳችሁ ጊዜ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሡአቸው። ያን ቦታ ርስት አድርጌ ለሎጥ ዘሮች ሰጥቻቸዋለሁ።”

20. ያም ደግሞ በዚያ ይኖሩ የነበሩት የረፋይማውያን ምድር እንደሆነ ይቈጠር ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሯቸው ነበር።

21. ዘምዙማውያን ብርቱዎች፣ ቊጥራቸው የበዛና እንደ ዔናቃውያን ቁመተ ረጃጅሞች ነበሩ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእነርሱ ፊት አጠፋቸው፤ እነርሱም አሳደዷቸው በምትካቸውም ሰፈሩበት።

22. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሖራውያንን ከፊታቸው ባጠፋ ጊዜ፣ በሴይር ለሚኖሩት የዔሳው ዘሮች ያደረገው ይህንኑ ነበር። እነርሱም አሳደው በማስወጣት ባስለቀቁት ስፍራ ላይ እስከ ዛሬ ይኖራሉ።

23. እስከ ጋዛ ድረስ ባሉት መንደሮች የኖሩትን ኤዋውያን በተመለከተም፣ ከከፍቶር ወጥተው የመጡት ከፍቶራውያን እነርሱን አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።

24. “አሁኑኑ ተነሡና የአርኖንን ወንዝ ተሻገሩ፤ እነሆ፣ የሐሴቦንን ንጉሥ፣ አሞራዊውን ሴዎንንና አገሩን በእጃችሁ ሰጥቻችኋለሁ፤ ምድሩን መውረስ ጀምሩ፤ ጦርነት ግጠሙት።

25. ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ፣ ማስደንገጣችሁና ማስፈራታችሁ እንዲያድ ርባቸው ከዚህች ከዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። ስለ እናንተ ሰምተው ይርበተበታሉ፤ ከእናንተ የተነሣም ይጨነቃሉ።”

26. ከቅዴሞት ምድረ በዳም ለሐሴቦን ንጉሥ ለሴዎን የሰላም ቃል እንዲያደርሱለት እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላክሁ፤

27. “በአገርህ አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን፤ ከዋናው መንገድ አንወጣም፤ ቀኝም ግራም አንልም።

28. የምንበላውን ምግብ፣ የምንጠጣውንም ውሃ፣ በጥሬ ብር ሽጥልን። በእግር እንድናልፍ ብቻ ፍቀድልን፤

29. በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮችና በዔር የሚኖሩ ሞዓባውያን እንዳደረጉልን ሁሉ፣ አንተም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጠን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን እስክንሻገር ድረስ እንደዚሁ አድርግልን።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 2