ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 2:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) “አሁኑኑ ተነሡና የዘሬድን ደረቅ ወንዝ ተሻገሩ” አለን፤ እኛም ወንዙን ተሻገርን።

14. ቃዴስ በርኔን ከለቀቅንበት ጊዜ አንሥቶ የዘሬድን ደረቅ ወንዝ እስከ ተሻገርንበት ጊዜ ድረስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ዐለፈ። በዚያን ጊዜም ለጦርነት ብቁ የሆኑት የዚያ ትውልድ ወንዶች ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እነርሱ አስቀድሞ በማለው መሠረት ከሰፈሩ ፈጽመው ዐለቁ።

15. ከሰፈር ፈጽሞ እስኪያጠፋቸውም ድረስ የእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ በእነርሱ ላይ ነበር።

16. በሕዝቡ መካከል የነበሩት የመጨረሻዎቹ ተዋጊዎች ከሞቱ በኋላ፣

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤

18. “የሞዓብ ዳርቻ ዔርን ዛሬውኑ ታልፋላችሁ።

19. ከየትኛውም የአሞናውያን ምድር ለእናንተ ርስት ስለማልሰጣችሁ፣ አሞናውያን ዘንድ በደረሳችሁ ጊዜ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሡአቸው። ያን ቦታ ርስት አድርጌ ለሎጥ ዘሮች ሰጥቻቸዋለሁ።”

20. ያም ደግሞ በዚያ ይኖሩ የነበሩት የረፋይማውያን ምድር እንደሆነ ይቈጠር ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሯቸው ነበር።

21. ዘምዙማውያን ብርቱዎች፣ ቊጥራቸው የበዛና እንደ ዔናቃውያን ቁመተ ረጃጅሞች ነበሩ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእነርሱ ፊት አጠፋቸው፤ እነርሱም አሳደዷቸው በምትካቸውም ሰፈሩበት።

22. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሖራውያንን ከፊታቸው ባጠፋ ጊዜ፣ በሴይር ለሚኖሩት የዔሳው ዘሮች ያደረገው ይህንኑ ነበር። እነርሱም አሳደው በማስወጣት ባስለቀቁት ስፍራ ላይ እስከ ዛሬ ይኖራሉ።

23. እስከ ጋዛ ድረስ ባሉት መንደሮች የኖሩትን ኤዋውያን በተመለከተም፣ ከከፍቶር ወጥተው የመጡት ከፍቶራውያን እነርሱን አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።

24. “አሁኑኑ ተነሡና የአርኖንን ወንዝ ተሻገሩ፤ እነሆ፣ የሐሴቦንን ንጉሥ፣ አሞራዊውን ሴዎንንና አገሩን በእጃችሁ ሰጥቻችኋለሁ፤ ምድሩን መውረስ ጀምሩ፤ ጦርነት ግጠሙት።

25. ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ፣ ማስደንገጣችሁና ማስፈራታችሁ እንዲያድ ርባቸው ከዚህች ከዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። ስለ እናንተ ሰምተው ይርበተበታሉ፤ ከእናንተ የተነሣም ይጨነቃሉ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 2