ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 2:12-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ሖራውያን ቀድሞ በሴይር ይኖሩ ነበር፤ የዔሳው ዘሮች ግን ከዚያ አሳደው አስወጧቸው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ርስት አድርጎ በሰጠው ምድር ላይ እስራኤል እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህም ሖራውያንን ከፊታቸው አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።

13. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) “አሁኑኑ ተነሡና የዘሬድን ደረቅ ወንዝ ተሻገሩ” አለን፤ እኛም ወንዙን ተሻገርን።

14. ቃዴስ በርኔን ከለቀቅንበት ጊዜ አንሥቶ የዘሬድን ደረቅ ወንዝ እስከ ተሻገርንበት ጊዜ ድረስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ዐለፈ። በዚያን ጊዜም ለጦርነት ብቁ የሆኑት የዚያ ትውልድ ወንዶች ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እነርሱ አስቀድሞ በማለው መሠረት ከሰፈሩ ፈጽመው ዐለቁ።

15. ከሰፈር ፈጽሞ እስኪያጠፋቸውም ድረስ የእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ በእነርሱ ላይ ነበር።

16. በሕዝቡ መካከል የነበሩት የመጨረሻዎቹ ተዋጊዎች ከሞቱ በኋላ፣

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤

18. “የሞዓብ ዳርቻ ዔርን ዛሬውኑ ታልፋላችሁ።

19. ከየትኛውም የአሞናውያን ምድር ለእናንተ ርስት ስለማልሰጣችሁ፣ አሞናውያን ዘንድ በደረሳችሁ ጊዜ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሡአቸው። ያን ቦታ ርስት አድርጌ ለሎጥ ዘሮች ሰጥቻቸዋለሁ።”

20. ያም ደግሞ በዚያ ይኖሩ የነበሩት የረፋይማውያን ምድር እንደሆነ ይቈጠር ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሯቸው ነበር።

21. ዘምዙማውያን ብርቱዎች፣ ቊጥራቸው የበዛና እንደ ዔናቃውያን ቁመተ ረጃጅሞች ነበሩ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእነርሱ ፊት አጠፋቸው፤ እነርሱም አሳደዷቸው በምትካቸውም ሰፈሩበት።

22. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሖራውያንን ከፊታቸው ባጠፋ ጊዜ፣ በሴይር ለሚኖሩት የዔሳው ዘሮች ያደረገው ይህንኑ ነበር። እነርሱም አሳደው በማስወጣት ባስለቀቁት ስፍራ ላይ እስከ ዛሬ ይኖራሉ።

23. እስከ ጋዛ ድረስ ባሉት መንደሮች የኖሩትን ኤዋውያን በተመለከተም፣ ከከፍቶር ወጥተው የመጡት ከፍቶራውያን እነርሱን አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።

24. “አሁኑኑ ተነሡና የአርኖንን ወንዝ ተሻገሩ፤ እነሆ፣ የሐሴቦንን ንጉሥ፣ አሞራዊውን ሴዎንንና አገሩን በእጃችሁ ሰጥቻችኋለሁ፤ ምድሩን መውረስ ጀምሩ፤ ጦርነት ግጠሙት።

25. ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ፣ ማስደንገጣችሁና ማስፈራታችሁ እንዲያድ ርባቸው ከዚህች ከዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። ስለ እናንተ ሰምተው ይርበተበታሉ፤ ከእናንተ የተነሣም ይጨነቃሉ።”

26. ከቅዴሞት ምድረ በዳም ለሐሴቦን ንጉሥ ለሴዎን የሰላም ቃል እንዲያደርሱለት እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላክሁ፤

27. “በአገርህ አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን፤ ከዋናው መንገድ አንወጣም፤ ቀኝም ግራም አንልም።

28. የምንበላውን ምግብ፣ የምንጠጣውንም ውሃ፣ በጥሬ ብር ሽጥልን። በእግር እንድናልፍ ብቻ ፍቀድልን፤

29. በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮችና በዔር የሚኖሩ ሞዓባውያን እንዳደረጉልን ሁሉ፣ አንተም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጠን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን እስክንሻገር ድረስ እንደዚሁ አድርግልን።”

30. ይሁን እንጂ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን እንድናልፍ አልፈቀደልንም። ምክንያቱም አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) አሁን እንዳደረገው ሁሉ እርሱን በእጃችሁ አሳልፎ ለመስጠት መንፈሱን አደንድኖት፣ ልቡንም አጽንቶት ነበር።

31. እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “እነሆ፣ ሴዎንንና አገሩን ለእናንተ አሳልፌ ልሰጣችሁ ተነሥቻለሁ፤ አሁንም እርሱን አሸንፋችሁ ምድሩን ለመውረስ ተነሡ” አለኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 2