ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 19:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥባቸውን አሕዛብ በሚደመስሳቸው ጊዜና አንተም እነርሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው በምትቀመጥበት ጊዜ፣

2. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር አማካይ ስፍራ፣ ሦስት ከተሞችን ለራስህ ለይ።

3. ሰው የገደለ ሁሉ እንዲሸሽባቸው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር መንገዶችን ሠርተህ፣ በሦስት ክፈላቸው።

4. በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ገድሎ ሕይወቱን ለማትረፍ ለሚሸሽ ሰው መመሪያው የሚከተለው ነው።

5. እነሆ፤ አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንጨት ለመቊረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፣ ዛፉን ለመጣል መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ወልቆ ባልንጀራውን በመምታት ቢገድለው፣ ያ ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል።

6. አለበለዚያ በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ቢገድል፣ መንገዱ ረጅም ከሆነ ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ይደርስበትና፣ መገደል የማይገባውን ሰው ሊገድል ይችላል።

7. ሦስት ከተሞችን ለራስህ እንድትለይ ያዘዝሁህ በዚሁ ምክንያት ነው።

8. ለአባቶችህ በመሐላ በገባላቸው ቃል መሠረት አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወሰንህን ሲያሰፋውና ለእነርሱ በሰጣቸው መሠረት ምድሪቷን ሁሉ ሲሰጥህ፣

9. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትወድና ምንጊዜም በመንገዱ እንድትሄድ ዛሬ የማዝህን እነዚህን ሕግጋት ሁሉ በጥንቃቄ የምትጠብቅ ከሆነ፣ በእነዚህ ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራለህ።

10. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር የንጹሕ ሰው ደም እንዳይፈስና በሚፈሰውም ደም በደለኛ እንዳትሆን ይህን አድርግ።

11. ይሁን እንጂ አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው፣ አድፍጦ ጥቃት ቢያደርስበት፣ ቢገድለውና፣ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፣

12. የሚኖርባት ከተማ ሽማግሌዎች ሰው ልከው ከከተማው ያስመጡት፤ እንዲገድለውም ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት።

13. አትራራለት፤ ነገር ግን መልካም እንዲሆንልህ የንጹሑን ደም በደል ከእስራኤል አስወግድ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 19