ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 12:4-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. በእነርሱ መንገድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አታምልኩ።

5. ዳሩ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፣ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ እሹ፤ ወደዚያም ስፍራ ሂዱ።

6. ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የፈቃዳችሁን ስጦታዎች፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ።

7. በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።

8. ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤

9. ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም።

10. ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፣ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል።

11. ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ።

12. እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት አድርጉ።

13. የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ።

14. ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝህን ሁሉ ጠብቅ፤

15. ሆኖም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ መጠን፣ በየትኛውም ከተማህ፣ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኵላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል።

16. ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።

17. የእህልህን፣ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ ወይም የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፣ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የፈቃድህን ስጦታ፣ ወይም የእጅህን ስጦታ፣ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም።

18. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፤ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይልሃል።

19. በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 12