ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 12:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ።

4. በእነርሱ መንገድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አታምልኩ።

5. ዳሩ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፣ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ እሹ፤ ወደዚያም ስፍራ ሂዱ።

6. ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የፈቃዳችሁን ስጦታዎች፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ።

7. በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።

8. ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤

9. ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም።

10. ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፣ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል።

11. ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ።

12. እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት አድርጉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 12