ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 12:20-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፣ ሥጋ አምሮህ፣ “ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ” በምትልበት ጊዜ፣ ያሰኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ።

21. ስሙን ለማኖር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፣ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፣ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ።

22. ሚዳቋ ወይም ድኵላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆኑትና ያልሆኑት ሊበሉ ይችላሉ።

23. ደሙን ግን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደም ሕይወት ስለ ሆነ፣ ሥጋን ከነሕይወቱ አትብላ።

24. ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።

25. በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላቸው አትብላው።

26. ነገር ግን የተቀደሱ ነገሮችህን ለመስጠት የተሳልሃቸውን ሁሉ ይዘህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ።

27. የሚቃጠል መሥዋዕትህን፣ ሥጋውንም ደሙንም በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ላይ አቅርብ። የመሥዋዕትህ ደም በአምላክህበእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን መብላት ትችላለህ።

28. በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ ለዘላለም መልካም እንዲሆንላችሁ፣ እኔ የምሰጥህን እነዚህን ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽማቸው።

29. የምትወሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፣

30. ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፣ “እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ” ብለህ በመጠየቅ እንዳ ትጠመድ ተጠንቀቅ።

31. አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚጸየፈውን ሁሉንም ዐይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳ ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ።

32. እኔ ያዘዝሁህን ሁሉ ጠብቅ፤ አትጨምር በት፤ አትቀንስለትም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 12