ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 12:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ሆኖም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ መጠን፣ በየትኛውም ከተማህ፣ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኵላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል።

16. ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።

17. የእህልህን፣ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ ወይም የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፣ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የፈቃድህን ስጦታ፣ ወይም የእጅህን ስጦታ፣ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም።

18. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፤ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይልሃል።

19. በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ።

20. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፣ ሥጋ አምሮህ፣ “ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ” በምትልበት ጊዜ፣ ያሰኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ።

21. ስሙን ለማኖር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፣ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፣ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ።

22. ሚዳቋ ወይም ድኵላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆኑትና ያልሆኑት ሊበሉ ይችላሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 12