ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 11:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. የእናንተ ዐይኖች ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) ያደረጋቸውን ሥራዎች ሁሉ አይተዋል።

8. ስለዚህ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ወደምትወርሷት ምድር ለመግባትና ለመያዝ ብርታት እንድታገኙ፣ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤

9. ለአባቶቻቸውና ለዘሮቻቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ሊሰጣቸው በማለላቸው፣ በዚያች ማርና ወተት በምታፈሰው ምድር ረጅም ዕድሜ ትኖሩ ዘንድ፣

10. የምትገባባት ምድር እንደ ወጣህባትና ዘርህን ዘርተህባት በእግርህ ውሃ እንዳጠጣሃት የአትክልት ቦታ እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም።

11. ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት።

12. ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚንከባከባት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ዐይን ምንጊዜም የማይለያት ናት።

13. ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች በታማኝነት ብትጠብቁ፣ ይኸውም አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ብትወዱና በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁም እርሱን በማገልገል በታማኝነት ብትጠብቁ፣

14. እህልህን፣ ወይንህንና ዘይትህን እንድትሰበስብ የበልጉንና የክረምቱን ዝናብ በምድርህ ላይ በየወቅቱ አዘንባለሁ።

15. በሜዳ ላይ ለከብቶችህ ሣር እሰጣለሁ፤ አንተም ትበላለህ፤ ትጠግባለህም።

16. ተጠንቀቁ አለበለዚያ ተታላችሁ ሌሎች አማልክትን ታመልካላችሁ፤ ትሰግዳላችሁም።

17. ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊጣ በላያችሁ ይነዳል፤ እርሱም ዝናብ እንዳይዘንብ፣ ምድሪቱም ፍሬ እንዳትሰጥ ሰማያትን ይዘጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ወዲያውኑ ትጠፋላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 11