ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 11:2-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ተግሣጽ ይኸውም ግርማውን፣ ብርቱ እጁንና የተዘረጋች ክንዱን ያዩትና የተለማመዱት ልጆቻችሁ ሳይሆኑ እናንተ እንደሆናችሁ ዛሬ አስታውሱ፤

3. በግብፅ መካከል፣ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንና በመላው አገሩ ላይ ያደረጋቸውን ምልክቶችና የሠራቸውን ነገሮች፣

4. በግብፃውያን ሰራዊት፣ በፈረሶቻቸውና በሠረገሎቻቸው ላይ፣ እናንተን ባሳደዷችሁ ጊዜ በቀይ ባሕር ውሃ እንዴት እንዳሰጠማቸውና እግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ እንዴት እንዳጠፋቸው አስታውሱ፤

5. ከምድረ በዳው አንሥቶ እዚህ እስከምትደርሱ ድረስ፣ ለእናንተ ያደረገላችሁን ያዩት ልጆቻችሁ አልነበሩም፤

6. የሮቤል ልጅ የኤልያብ ልጆች የሆኑትን ዳታንና አቤሮንን ከነቤተ ሰቦቻቸው፣ ከነድንኳናቸውና ከነእንስሳታቸው በመላው እስራኤል መካከል ምድር እንዴት አፏን ከፍታ እንደዋጠቻቸው እነርሱ አላዩም።

7. የእናንተ ዐይኖች ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) ያደረጋቸውን ሥራዎች ሁሉ አይተዋል።

8. ስለዚህ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ወደምትወርሷት ምድር ለመግባትና ለመያዝ ብርታት እንድታገኙ፣ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤

9. ለአባቶቻቸውና ለዘሮቻቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ሊሰጣቸው በማለላቸው፣ በዚያች ማርና ወተት በምታፈሰው ምድር ረጅም ዕድሜ ትኖሩ ዘንድ፣

10. የምትገባባት ምድር እንደ ወጣህባትና ዘርህን ዘርተህባት በእግርህ ውሃ እንዳጠጣሃት የአትክልት ቦታ እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም።

11. ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 11