ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 10:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀርጸህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ላይ ውጣ፤ ታቦትም ከዕንጨት ሥራ።

2. እኔም አንተ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት በእነዚህኞቹ ጽላቶች ላይ እጽፋቸዋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታኖራቸዋለህ።”

3. ስለዚህ ከግራር ዕንጨት ታቦት ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀረጽሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጆቼ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ።

4. እግዚአብሔር (ያህዌ) በስብሰባው ቀን፣ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የተናገራቸውንና ቀድሞ ጽፎአቸው የነበሩትን ዐሥሩን ትእዛዛት በእነዚህ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ።

5. ከዚያም ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘኝ መሠረት በሠራሁት ታቦትም ውስጥ፣ ጽላቶቹን አስቀመጥኋቸው፤ አሁንም እዚያ ናቸው።

6. እስራኤላውያን ከብኤሮት ብኔያዕቃን፣ የያዕቃን ልጆች ከቈፈሯቸው የውሃ ጒድጓዶች ተነሥተው ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም በዚያ ቦታ ሞቶ ተቀበረ፤ ልጁ አልዓዛር በእርሱ ምትክ ካህን ሆነ።

7. ከዚያም ተነሥተው ጒድጎዳ ወደተባለ ስፍራ፣ ቀጥሎም የውሃ ፈሳሾች ወዳሉባት ዮጥባታ ወደምትባል ምድር ተጓዙ።

8. በዚያን ጊዜ፣ ዛሬም እንደሚያደርገው ያገለግል ዘንድ፣ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት እንዲቆምና በስሙ እንዲባርክ የእግዚአብሔርንም (ያህዌ) የኪዳኑን ታቦት እንዲሸከም እግዚአብሔር (ያህዌ) የሌዊን ነገድ ለየ።

9. ሌዋዊ በወንድሞቹ መካከል ድርሻም ሆነ ርስት የሌለው ከዚህ የተነሣ ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገረው መሠረት ርስቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 10