ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 1:35-46 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. “ለቀደሙት አባቶቻችሁ ለመስጠት የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር፣ ከዚህ ክፉ ትውልድ አንድም ሰው አያያትም፤

36. ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በስተቀር የሚያያት የለም፤ እርሱ ያያታል፤ እግዚአብሔርን (ያህዌ) በፍጹም ልቡ ስለ ተከተለ፣ የረገጣትን ምድር ለእርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።”

37. በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔን ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “አንተም ብትሆን አትገባባትም።

38. ረዳትህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ይገባባታል፤ ምድሪቱን እንዲወርሱ እስራኤልን የሚመራ እርሱ ስለ ሆነ፣ አበረታታው።

39. ይማረካሉ ያላችኋቸው ታናናሾች፣ ክፉና በጎውን ለይተው የማያውቁት ልጆቻችሁ ምድሪቱን ይገቡባታል፤ ለእነርሱም እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሷታል።

40. እናንተ ግን፣ ተመልሳችሁ ወደ ቀይ ባሕር የሚወስደውን መንገድ ይዛችሁ ወደ ምድረ በዳው ተጓዙ።”

41. እናንተ፣ “እግዚአብሔርን (ያህዌ) በድለናል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘንም መሠረት ወጥተን እንዋጋለን ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ወደ ተራራማው አገር መሄድ ቀላል መስሎ ስለ ታያችሁ፣ እያንዳንዳችሁ የጦር መሣሪያችሁን ታጥቃችሁ ተነሣችሁ።

42. እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን፣ “እኔ ከእናንተ ጋር አልሆንምና ወጥታችሁ እንዳትዋጉ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትነሣላችሁ ብለህ ንገራቸው” አለኝ።

43. እኔም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁም፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐምፃችሁ፤ በትዕቢታችሁ ወደ ኰረብታማዪቱ አገር ዘመታችሁ።

44. በነዚያ ኰረብቶች ላይ የሚኖሩት አሞራውያን ሊወጓችሁ ወጡ፤ እንደ ንብ ሰራዊትም ሆነው አባረሯችሁ፤ ከሴይር አንሥቶ እስከ ሔርማ ድረስ አሳደው መቷችሁ።

45. እናንተም ተመልሳችሁ መጥታችሁ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አለቀሳችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) ልቅሶአችሁን አልሰማም፤ አላዳመጣችሁምም።

46. ስለዚህ ያን ያህል ጊዜ በማጥፋት በቃዴስ ብዙ ቀን ቈያችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 1