ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 1:25-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን።

26. እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ።

27. በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጒረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብፅ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን፣ በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው።

28. ታዲያ ወዴት መሄድ እንችላለን? ወንድሞቻችን፣ ‘ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎችና ቁመተ ረጃጅሞች፣ ከተሞቹም ትልልቆችና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የዔናቅን ልጆች አይተናቸዋል’ ሲሉ እንድንፈራ አድርገውናል።”

29. እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም።

30. በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዚህ በፊት ዐይናችሁ እያየ በግብፅ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፣ አሁንም ለእናንተ ይዋጋል፤

31. በምድረ በዳው እንደ አደረገው ሁሉ። በዚያም አባት ልጁን እንደሚሸከም፣ እናንተን አምላካችሁእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እዚህ ስፍራ እስክትደርሱ በመጣችሁበት መንገድ ሁሉ እንዴት እንደ ተሸከማችሁ አይታችኋል።”

32. ይህም ሆኖ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አልታመናችሁም፤

33. በጒዞ ላይ ሳላችሁ የምትሰፍሩባቸውን ቦታዎች ለመፈለግና የምትሄዱበትን መንገድ ለማሳየት እርሱ ሌሊት በእሳት፣ ቀን በደመና ይመራችሁ ነበር።

34. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እናንተ ያላችሁትን በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ ማለም፤

35. “ለቀደሙት አባቶቻችሁ ለመስጠት የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር፣ ከዚህ ክፉ ትውልድ አንድም ሰው አያያትም፤

36. ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በስተቀር የሚያያት የለም፤ እርሱ ያያታል፤ እግዚአብሔርን (ያህዌ) በፍጹም ልቡ ስለ ተከተለ፣ የረገጣትን ምድር ለእርሱና ለዘሮቹ እሰጣለሁ።”

37. በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔን ተቈጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “አንተም ብትሆን አትገባባትም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 1