ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘዳግም 1:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ዓረባ በተባለው ምድረ በዳ ከሱጰ ትይዩ፣ በፋራንና በጦፌል፣ በላባን፣ በሐጼሮትና በዲዛሃብ መካከል ሳሉ፣ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የተናገረው ቃል ይህ ነው።

2. (በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ዐሥራ አንድ ቀን ያስሄዳል)።

3. በአርባኛው ዓመት፣ በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን እስራኤላውያንን በሚመለከት እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ ሙሴ ለእነርሱ ነገራቸው።

4. ይህ የሆነው በሐሴቦን ይገዛ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንና በአስታሮት ይገዛ የነበረውን የዐግን ንጉሥ ባሳንን በኤድራይ ድል ካደረገ በኋላ ነው።

5. ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሞዓብ ምድር ሳሉ፣ ሙሴ ይህን ሕግ እንዲህ እያለ መግለጥ ጀመረ፤

6. “እግዚአብሔር አምላካችን (ያህዌ ኤሎሂም) በኮሬብ እንዲህ አለን፤ ‘እነሆ በዚህ ተራራ ለረጅም ጊዜ ቈይታችኋል።

7. ሰፈር ነቅላችሁ ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ጒዞ ቀጥሉ፤ ከዚያም በዓረባ፣ በተራሮቹ፣ በምዕራብ ኰረብታዎች ግርጌ፣ በኔጌብና በባሕሩ ዳርቻ ወዳሉት አጐራባች ሕዝቦች ሁሉ ሂዱ፤ እንዲሁም ወደ ከነዓናውያን ምድርና ወደ ሊባኖስ፣ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ዝለቁ።

8. እነሆ፤ ይህችን ምድር ሰጥቻችኋለሁ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ከእነርሱም በኋላ ለዘሮቻቸው ሊሰጥ የማለላቸውን ምድር ገብታችሁ ውረሱ።”

9. “እኔም በዚያን ጊዜ እንዲህ አልኋችሁ፤ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤

10. አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቊጥራችሁን ጨምሮአል፤ ስለዚህ ዛሬ እናንተ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘዳግም 1